Ethiopia

በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ምግብን መሠረት ያደረገ የአመጋገብ መመሪያ ይፋ ተደረገ::

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 7፣ 2014 በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ምግብን መሠረት ያደረገ የአመጋገብ መመሪያ ይፋ ተደረገ:: መመሪያውን በኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስተባባሪነት የጤና ሚኒስቴር፣ የግብርና ሚኒስቴር፣ የትምህርት ሚኒስቴርና አጋር አካላት ናቸው በጋራ ያዘጋጁት፡፡ የማዕከላዊ ስታቲስቲክስ የ2019 ጥናት እንደሚያመለክተው በሀገራችን 54 በመቶ የሚሆኑ ቤተሰቦች እንዲመገቡ ከሚመከረው ሰባት የምግብ ምድቦች ውስጥ ከአራት በታች የሚመገቡ
መሆናቸው ተረጋግጧል ነው የተባለው፡፡


በተለይም ህፃናትና ሴቶች አነስተኛ ቁጥር ያለው የምግብ ምድብ ስብጥር እንደሚመገቡ ይህም ለመቀንጨርና ሌሎች የጤና እክሎች መንስኤ ሊሆን እንደሚችል የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ ተናግረዋል፡ መመሪያው የአመጋገብ ሁኔታን ለማሻሻል የአመጋገብ መስፈርቶችን ያማከለ እና በንጥረ ነገሮች የበለፀጉ ምግቦችን ያካተተ የአመጋገብ ስርዓትን ለመተግበር መዘጋጀቱንም ተናግረዋል።


የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሀኑ ነጋ በበኩላቸው ምግብን መሠረት ያደረገ የስነ አመጋገብ ስርዓትን በስርዓተ ትምህርት ውስጥ በማካተት ሀገር አቀፍ የአመጋገብ ባህልን የማሻሻል ተልዕኮውን ለማሳካት የተለያዩ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡ ሀገሪቱ ያስቀመጠቸውን የምግብ ምርታማነትን ለማሻሻልና ሀገር በቀል የትምህርት ቤት ምገባ መርሀ-ግብርን በየአመቱ ለማስፋፋት በዚህ ዓመት ከ1.9 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች የመርሀ-ግብሩ ተጠቃሚዎች እንደሚሆኑም ተናግረዋል፡፡


የግብርና ሚኒስትር ዴኤታው ዶክተር ፍቅሩ ረጋሳ መመሪያው የጋራ ሀላፊነትን በመውሰድ ስራን ወደ ተግባር ለመቀየር የሚያስችል አሰራር ይዞ የቀረበ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ኢትዮጵያ ይህን መመሪያ ስታዘጋጅ በአፍሪካ ከስምንቱ የአመጋገብ መመሪያ ካላቸው ሀገራት መካከል አንዷ እንደሚያደርጋት ከጤና ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያሳያል፡፡

Related Articles

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Back to top button