AfricaEthiopiaSocial

የኢትዮጵያ አየርመንገድ አውሮፕላን በረራዎች በከባድ አደጋ ውስጥ ናቸው”

ይህንን ያለው የኬንያ አየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች ማህበር ነው።
አርትስ 26/12/2010


ማህበሩ ከሁለት ቀናት በፊት ለኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን በጻፈው ደብዳቤ “በሰሞኑ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራዎች ለከባድ አደጋ የሚዳርጉ የአየር ደህንነት ክፍተቶች እየታዩ ነው” ብሏል።
በኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን እና በበረራ ደንነት ተቆጣጣሪዎች መካከል የተካረረው አለመግባባት በዚሁ ከቀጠለ ለቀጠናው የአየር በረራ ደህንነት ስጋት መፈጠሩ አይቀርም በማለትም አስጠንቅቋል።
ማህበሩ በላከው በዚሁ ደብዳቤ ላይ የኢትዮጵያ አየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች የስራ ማቆም አድማ ከጀመሩ በኋላ የተከሰቱ የቁጥጥር እና መረጃ ማስተላለፍ ችግሮች ለአውሮፕላኖች መጥፋት እና ለበረራ አደጋ መከሰት ምክንያት ሊሆኑ እንደሚችሉ ስጋቱን ገልጿል።
ሰሞኑን ከኢትዮጵያ ወገን በሚታየው የአየር ትራፊክ ቁጥጥር መረጃ ስህተት የተነሳ ወደኬንያ በሚበሩ የኢትዮጵያ አውሮፕላኖች ላይ ታይተዋል ያላቸውን ስምንት ችግሮችም ዘርዝሯል።
ተደጋጋሚ የአውሮፕላኖች ማረፊያ ሰዓት ግምት ስህተት፣ የመዳረሻ አየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች ሳያውቁትና በቂ ቅንጅት ሳይደረግ የኢትዮጵያ አውሮፕላኖች ወደስፍራው ማምራት እንዲሁም በበረራ ላይ ያሉ አውሮፕላኖች ሞዴል እና ስም ከሚላከው መረጃ ጋ ተመሳሳይ አለመሆን ማህበሩ በዋናነት የጠቀሳቸው ችግሮች ናቸው።
የኢትዮጵያ አውሮፕላኖች ወደኬንያ ይገቡበታል ተብሎ ከሚጠበቀው የበረራ መስመር በተቃራኒ መምጣትና ይበሩበታል ተብሎ ከሚጠበቀው ርቀት ከፍ ወይም ዝቅ ብሎ መብረር “የከፋ አደጋ የሚያስከትሉ ናቸው” ካላቸው ችግሮች ውስጥ መድቧቸዋል።
የሚመለከታቸው ወገኖች ሁሉ በአቪየሽኑ እና በሰራተኞቹ መካከል የተፈጠረውን መካረር በማርገብ የሃገሪቱን የበረራ ደህንነት አስተማማኝ ለማድረግ እንዲሰሩም ጥሪ አቅርቧል።
ከአንድ መቶ በላይ የሚሆኑ በቦሌ አለም አቀፍና በክልል አየር ማረፊያዎች የሚሰሩ የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች “ላለፉት ስምንት አመታት ስናቀርብ የቆየነው የደመወዝና ጥቅማ ጥቅም ጥያቄ ምላሽ አላገኘም” በማለት የስራ ማቆም አድማ ላይ መሆናቸው ይታወቃል።
የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን በአድማው ላይ የተካፈሉ ሰራተኞች ይቅርታ ከጠየቁ ወደስራ ገበታቸው መመለስ እንደሚችሉ ቢያሳውቅም ሰራተኞቹ ግን “ከትራንስፖርት ሚኒስትሩ እና ከመንግስት አካላት ጋ ተነጋግረን ችግሮቻችን እንደሚፈቱ ከተገለጸልን በኋላ ወደስራ ገበታችን እንመለስ ስንል ባለስልጣኑ “የይቅርታ ቅድመ ሁኔታ አዘጋጅቶ ጠበቀን” ይላሉ።
ከቅሬታ አቅራቢ ሰራተኞች አንዱ የሆኑት አቶ ቁምላቸው መካሻ ትናንት ከኢቲቪ ዜና ጋ በነበራቸው ቆይታ “በይቅርታ ፎርሙ ላይ የተዘረዘሩት አንቀጾች አሳሪ በመሆናቸው ሰራተኛው ለመፈረም አልተስማማም” ብለዋል።
የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኮሎኔል ወሰንየለህ ሁነኛው በበኩላቸው “ዛሬ ከስህተቱ ያልተማረ ሰራተኛ ነገ በአግባቡ ይሰራል ተብሎ አይታመንም። በማን ሃላፊነት እዚህ ቦታ ላይ ኢትዮጵያን ወክሎ መቀመጥ ይችላል? በፍጹም ሊሆን አይችልም” በማለት ይቅርታ መጠየቅ ግዴታ መሆኑን አስምረውበታል።
በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ አውሮፕላኖች አየር ትራፊክ ቁጥጥር ስራ እየተከናወነ ያለው ጡረታ በወጡና ይህንን ክፍተት እንዲሞሉ ጥሪ በቀረበላው የቀድሞ የአቪየሽኑ ሰራተኞች ነው።

Related Articles

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Back to top button