Politics

በምዕራብ ኦሮሚያ ሶስት ዞኖች 18 የመንግስትና የግል ባንኮች ተዘረፉ

በምዕራብ ኦሮሚያ ሶስት ዞኖች 18 የመንግስትና የግል ባንኮች ተዘረፉ

በኦሮሚያ ክልል ምእራብ ወለጋ፣ ቄለም እና ሆሮ ጉዱሩ ዞኖች በሚገኙ 18 የመንግስት እና የግል ባንኮች ላይ ዝርፊያ መፈፀሙን የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት አስታውቋል።

የክልሉ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው ዝርፊያው የተፈጸመው በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና በኦሮሚያ ህብረት ስራ ባንክ ቅርንጫፎች እንዲሁም በኦሮሚያ ብድርና ቁጠባ ተቋም ላይ ነው።

ከባንኮች ዝርፊያ ባለፈም የተለያዩ የግል እና የመንግስት ንብረቶች ላይ ጉዳት ደርሷል ብሏል ቢሮው በመግለጫው ።

ከዘረፋው በተጨማሪ በዞኖቹ የመንግስት መስሪያ ቤቶች መቃጠላቸውን የገለጸው ቢሮው ቁጥራቸው 10 የሚደርሱ የመንግስት እና የግል ተሽከርካሪዎችም በተመሳሳይ ተቃጥለዋል ብሏል።

በዞኖቹ የተለያዩ የስራ ሰነዶችን የማቃጠል እና የማውደም፣ የመንግስት ተሽከርካሪ እና የግል ንብረቶች ዝርፊያ እንዲሁም መንገድ በመዝጋት የህዝቡን የመንቀሳቀስ መብት የመገደብ ተግባር ተፈፅሟል ብሏል።

በዚህ ህገ ወጥ ተግባር ላይ ተሳትፈዋል ተብለው የተጠረጠሩ ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር የማዋል ስራ እየተሰራ መሆኑንም ነው ቢሮው በመግለጫው ያስታወቀው።

ይህንን የወንጀል ተግባር በማቀነባበር እና በመፈፀም የተጠረጠሩ ግለሰቦችም በህግ ቁጥጥር ስር እየዋሉ ነው ብሏል።

በአሁኑ ወቅት የህግ የበላይነትን ለማስከበር እና የህዝቡን ደህንነት ለማረጋገጥ እየተሰራ ባለው ስራም በምእራብ ኦሮሚያ ያለው የሰላም ሁኔታ እየተሻሻለ መጥቷል ያለው መግለጫው አሁን የተገኘው ሰላም ቀጣይነት እንዲኖረውም የአካባቢው ህዝብ እና መንግስት ከፀጥታ አካላት ጋር በጋራ በመሆን እየሰሩ ነው ብሏል።

Related Articles

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Back to top button