Uncategorized

የአቶ በረከት ስምኦንና አቶ ታደሰ ካሳ ጉዳይ በክልሉ ፍርድ ቤት እንደሚታይ ተገለፀ

የአቶ በረከት ስምኦንና አቶ ታደሰ ካሳ ጉዳይ በክልሉ ፍርድ ቤት እንደሚታይ ተገለፀ፡፡

በጥረት ኮርፖሬት ላይ ከደረሰ የሀብት ብክነት ወንጀል ጋር በተያያዘ ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር የዋሉት አቶ በረከት ስምኦን እና አቶ ታደሰ ካሳ ጉዳይ በክልል ፍርድ ቤት እንደሚታይ የአማራ ክልል ፀረ ሙስና ኮሚሽን ገለፀ።

የአማራ ክልል ፀረ ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ዝግአለ ገበየሁ  ሁለቱ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለው ወደ ባህር ዳር ተወስደዋል ብለዋል።

የተጠረጠሩበት ወንጀል የተፈፀመውም በክልሉ በመሆኑ ጉዳያቸው በክልሉ ፍርድ ቤት እንደሚታይ ነው ኮሚሽነሩ ያስታወቁት።

በእስካሁኑ ሂደት በግለሰቦቹ ላይ ክስ ለመመስረት የሚያስችለኝን ከበቂ በላይ ማስረጃ ሰብስቤያለሁም ብሏል ኮሚሽኑ ።

በዚህም የጥረት ኮርፖሬሽን ብክነት ተፈጽሞብኛል ብሎ በሰጠው ጥቆማ መሰረት ከአምስት ኩባንያዎች የአክስዮን ግዢ ጋር በተያያዘ የተፈጸመ ብልሹ አሰራር ኦዲት ተደርጓል።

በኦዲት ግኝቱ መሰረትም ክስ ሊያስመሰርት የሚችል ማስረጃዎች በመገኘታቸው ምክንያት በጉዳዩ ዋነኛ ተሳታፊ ናቸው ተብለው ተጠርጥረው መያዛቸውን ገልጸዋል።

የሌሎች ሁለት ኩባንያዎች የኦዲት ግኝም በመመርመር ላይ እንደሚገኝ ኮሚሽነሩ ተናግረዋል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ በኃላፊነት በነበሩበት ወቅት ጥረት በመሰረታቸው ስድስት ኩባንያዎች ላይ የተለያዩ ብልሹ አሰራሮችን መፈጸማቸውን አብራርተዋል።

ስድስቱ ኩባንያዎች ሲመሰረቱም የአዋጭነት ጥናት ያለመካሄዱን የጠቀሱት ኮሚሽነሩ፥ 35 ሚሊየን ብር ለነዚህ ኩባንያዎች ግዢ መውጣቱን ገልጸዋል።

ግዢያቸው ከተፈጸመ በኋላም ወደ ስራ ያልገቡ ሲሆን፥ ጥረትንም ለተጨማሪ ኪሳራ ዳርገውታል ነው ያሉት ኮሚሽነሩ።

ጥረት ኮርፖሬሽን በአጋርነት ከሚሰራቸው ኩባንያዎች ጋርም ከኮርፖሬሽኑ የፋይናንስ አሰራርና ህግ ውጪ 7 ሚሊየን ብር ለሁለት ኩባንያዎች መሰጠታቸውን ጠቅሰዋል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ በሦስት ግለሰቦች ለሚተዳደር አንድ የማዕድን ኩባንያ ላወጣው የ1000 ብር የአክስዮን ዋጋ ጥረት በአንጻሩ 2 ሺህ 200 ብር እንዲገዛ መደረጉን ጠቅሰዋል።

በዚህም ግለሰቦቹን የ4 ሚሊየን 320 ሺህ ብር ተጠቃሚ ያደረገ ሲሆን፥ ጥረትን ለኪሳራ ዳርጓል ብለዋል።

በተጨማሪም ለካፒታል ዕድገት ለሀገር ውስጥ ገቢ መክፈል የነበረበትን 1 ሚሊየን 296 ሺህ ባለመክፈሉ ጥረትን ባለዕዳ ማድረጉን አብራርተዋል።

ለፋብሪካ ግንባታ የሚውል የ17 ሚሊየን ብር ግብዓት ተገዝቶ እስከአሁን ስራ ላይ ባለመዋሉ ለብልሽት መዳረጉን ጠቅሰዋል።

ኮሚሽነር ዝግአለ እንዳሉት ከዚህ ጋር በተያያዘ በቁጥጥር ስር የሚውሉ ሌሎች ተጠርጣሪዎች አሉ ኤፍ.ቢ.ሲ እንደዘገበው።

 

Related Articles

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Back to top button