EthiopiaSocial

ኢትዮጵያ የ74ኛው የተመድ ጠቅላላ ጉባዔ ምክትል ፕሬዚዳንት ሆና ተመረጠች

ኢትዮጵያ የ74ኛው የተመድ ጠቅላላ ጉባዔ ምክትል ፕሬዚዳንት ሆና ተመረጠች
የተመድ ጠቅላላ ጉባዔ ለ74ኛው ጠቅላላ ጉባዔ በፕሬዚዳንትነት እና በምክትል ፕሬዚዳንትነት የሚያገለግሉ ሀገራትን መርጧል። በዚህም ምርጫ ጠቅላላ ጉባዔውን ናይጄሪያ በፕሬዚዳንትነት ኢትዮጵያን ጨምሮ አምስት ሀገራት ደግሞ በምክትል ፕሬዚዳንትነት እንዲያገለግሉ በሙሉ ድምጽ ተመርጠዋል።

ኢትዮጵያ በምክትል ፕሬዚዳንትነት የምታገለግልበትና እ.ኤ.አ. ከመስከረም ወር 2019 ጀምሮ የሚጀመረው 74ኛው ጠቅላላ ጉባዔ በከፍተኛ ደረጃ የተዘጋጁና የሀገራት መሪዎች የሚሳተፉባቸው ታላላቅ ስብሰባዎች የሚካሄዱበት ጉባዔ ነው።

ከነዚህ ታላላቅ ጉባዔዎች መካከልም በተመድ ዋና ጸሐፊ አዘጋጅነት የሚካሄደውና እ.ኤ.አ. መስከረም 23 ቀን 2019 የሚደረገው የአየር ንብረት ለውጥ የድርጊት ከፍተኛ ጉባዔ የሚገኝበት ሲሆን ሀገራችን በዋና ጸሀፊው ከተለዩት ዘጠኝ የድርጊት አቅጣጫዎች መሀከል የታዳሽ ኃይል እና የኢነርጂ ሽግግር የድርጊት አቅጣጫን ከዴንማርክ ጋር በጋራ እንድትመራ በመመረጥ ሰፊ ስራዎችን እየሰራችበትና በጠቅላላ ጉባዔው ወቅትም ይህንኑ የመሪነት ሚናዋን የምታሳይበት ይሆናል።

ከዚህ ጎን ለጎን እ.ኤ.አ. መስከረም 24 ቀን 2019 በጠቅላላ ጉባዔ ደረጃ የሚደረገው የዘላቂ ልማት ግቦች የፖለቲካ ጉባዔ፣ እ.ኤ.አ. መስከረም 26 ቀን 2019 በጠቅላላ ጉባዔ ደረጃ የሚደረገው የፋይናንስ ለልማት ስብሰባ፣ እንዲሁም እ.ኤ.አ. መስከረም 23 ቀን 2019 የሚካሄደው ሁሉን አቀፍ የጤና ሽፋን ከፍተኛ ጉባዔ በ74ኛው ጠቅላላ ጉባዔ ወቅት ትኩረት የሚሰጣቸው ናቸው።

ከእነዚህ ታላላቅ ስብሰባዎች በተጨማሪ ተመራጭ ፕሬዚዳንቶችና ምክትል ፕሬዚዳንቶች ዓመቱን ሙሉ የሚካሄዱ ስብሰባዎችን የመምራትና የማስተባበር ኃላፊነቶች እንደሚኖርባቸው ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የቃል አቀባይ ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

Related Articles

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Back to top button