Uncategorized

በጅቡቲ ወደብ በኩል ወደ ኢትዮጵያ በሽፋን የገባው ሁለት ኮንቴነር ህገወጥ የጦር መሳሪያ በቁጥጥር ስር ዋለ::

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 2፣ 2012 አለም አቀፍ የጦር መሳሪያ አዘዋዋሪ ቡድን በጅቡቲ ወደብ በኩል ወደ ኢትዮጵያ በሽፋን ያስገባው ሁለት ኮንቴነር ህገወጥ የጦር መሳሪያ በቁጥጥር ስር እንዲውል ማድረጉን የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

መነሻውን ከቱርክ ሜርሲን ወደብ ያደረገው ህገወጥ የጦር መሳሪያው፤ በጅቡቲ ወደብ በኩል ወደ ኢትዮጵያ በሽፋን ገብቶ በቁጥጥር ስር የዋለው፤ በወደቡ ለአምስት ወራት ያህል በድብቅ ተቀምጦ፤ በረቀቀ መንገድ ወደ ሀገር ውስጥ ከገበ በኋላ መሆኑን ለፋና በላከው መግለጫ አመልክቷል።

ግምታቸው ከግማሽ ቢሊየን ብር በላይ የሆኑ ከ18 ሺህ በላይ ቱርክ ሰራሽ ሽጉጦች ጋር መያዛቸውን የጠቆመው መግለጫው፤ ለሽፋን እንዲያገለግሉ ታስቦ የተዘጋጁ የኤሌክትሮኒክስ እቃዎችን በውስጣቸው የያዙ 229 ካርቶኖችም ጭምር በቁጥጥር ስር ውለዋል።

ይህ ህገወጥ የጦር መሳሪያ ወደ ሀገር ውስጥ ቢሰራጭ ኖሮ በሀገርና በህዝብ ደህንነት ላይ ከፍተኛ አደጋና ስጋት ይደቅን እንደነበር የገለፀው መግለጫው፤ የጦር መሳሪያውን በቁጥጥር ስር የማዋል ኦፕሬሽኑ በስኬት በመጠናቀቁ ምክንያት ሀገርና ህዝብን ከተደቀነበት ጥፋት የመታደግ ተልዕኮውን በአግባቡ መወጣት ተችሏል ብላል።

ወደ አገሪቱ የገባውን የጦር መሳሪያ ተቀብለው በአገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች ለማሰራጨት የተዘጋጁ 24 ተጠርጣሪዎችን የጦር መሣሪያውን ለመረከብ በዝግጅት ላይ እንዳሉ በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ተደርጎ ምርመራው በሚመለከተው አካል መቀጠሉን መግለጫው አመልክቷል።

ኤጀንሲው ድንበር ተሸጋሪ የጦር መሳሪያ አዘዋዋሪዎችን እና የጦር መሳሪያውን በቁጥጥር እንዲውል ከማድረጉም በተጨማሪ ከጅቡቲ፣ ከሱዳን፣ ከሊቢያ፣ ከቱርክ እና ከአሜሪካ አቻ የመረጃ ተቋማት ጋር የመረጃ ልውውጥ በማድረግ ድንበር አቋርጠው ወደ ሀገር ውስጥ ያስገቡ እና ያልተያዙትን በቁጥጥር ስር ለማዋል የክትትልና የቁጥጥር ስራው መጠናከሩን በመግለጫው አስታውቋል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘም 7 የተለያዩ ሃገራት ዜግነት ያላቸው የውጭ ተጠርጣሪዎች ሲኖሩ ከእንዚህ ውስጥም 2 የሱዳን ዜግነት ያለቸው ተጠርጣሪዎች ከሱዳን የመረጃ ተቋም ጋር መረጃ በመለዋወጥ በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ተደርጓል። ሌሎች በቁጥጥር ስር ያልዋሉ ተጠርጣሪዎችን ከሊቢያ፣ ከጁቡቲ፣ ከሱዳን፣ ከቱርክና ከአሜሪካ አቻ የመረጃ ተቋማት ጋር መረጃ በመለዋወጥ ግለሰቦችን በቁጥጥር ሰር ለማዋል የትብብር ስራ መጀመሩንም መስሪያ ቤቱ አስታውቋል።

የጦር መሳሪያው በቁጥጥር ስር እንዲውል በወሰዳቸው እርምጃዎች የጉምሩክ ኮሚሽን፣ የፌደራል፣ የኦሮሚያ፣ የአማራ እና የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽኖች ላደረጉት ከፍተኛ ድጋፍ ምሰጋና አቅርቧል። የህብረተሰቡም የተለመደ ትብብርና ድጋፍ ለኦፕሬሽኑ መሳካት ከፍተኛ ሚና እንደነበርውም አክላል።

በቀጣይም ህብረሰተሰቡ እየረቀቀ እና አየተባባሰ የመጣውን አገርና ህዝብን ሰላም የሚያናጋውን ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ወንጀል ለመካለካል በሚደረገው ጥረት ወስጥ እያበረከተ ያለውን አስተዋፅኦ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርቧል።

 

Related Articles

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Back to top button