AfricaEthiopia

በህዳሴው ግድብ ውሃ አሞላል ላይ ተጽዕኖ ለመፍጠር በግብጽ በኩል የተፈፀመዉን የሳይበር ጥቃት ማክሸፉን ኤጀንሲዉ አስታወቀ፡፡

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 16፣ 2012 በህዳሴው ግድብ ውሃ አሞላል ላይ ተጽዕኖ ለመፍጠር በግብጽ በኩል የተፈፀመዉን የሳይበር ጥቃት ማክሸፉን ኤጀንሲዉ አስታወቀ፡፡ጥቃቱ ቢፈጸም ኖሮ ፤ በሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ፤ ፖሊቲካዊ እና ስነ ልቦናዊ ጉዳት ሊያስከትል ይችል እንደነበር የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ አስታዉቋል፡፡ኤጀንሲዉ ሰኔ 10፣ 12 ፣ 13 እና 14 2012 ዓ.ም መቀመጫቸዉን ግብጽ ያደረጉ የሳይበር ወንጀለኞች በኢትዮጵያ የኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ጫና ለመፍጠር የሳይበር ጥቃት አድርሰዉ ነበር ብሏል፡፡የሳይበር ጥቃት ሙከራው የተቃጣው ሳይበር ሆሩስ ግሩፕ አኑቢስ ዶት ሃከር እና ሴኪዩሪቲ ባይ ፓስ በተባሉ የሳይበር አጥቂዎች አማካይነት መሆኑን ኤጀንሲው ገልጿል፡፡ወንጀለኞቹ ለረጅም ጊዜ ሲዘጋጁ የቆዩ እና ኤጀንሲው ሲከታተላችው የነበሩ ሲሆን በይበልጥ አርብ ሰኔ 12/2012 እና ቅዳሜ ሰኔ 13/2012 ከፍተኛ የሚባል የሳይበር ጥቃት ሙከራዎች አድርገዋል፡፡

 

የሳይበር ጥቃት አድራሾቹ፤ የ13 የመንግስት፣ 4 መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማትን የድረ-ገጽን የማስተጓጎል ሙከራ ማድረጋቸውን አስታውቋል፡፡የሳይበር ጥቃት ሙከራው በሀገሪቱ የመንግስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት፤ የደህንነት መስሪያ ቤቶች እና የግል ድርጅቶች ድረ-ገጽ ላይ ያነጣጠረ ነበር፡፡ሳይበር ሆሩስ ግሩፕ፣ አኑቢስ ዶት ሃከር እና ሴኪዩሪቲ ባይ ፓስ የሳይበር ጥቃት አድራሽ ቡድኖች ሃላፊነቱን የወሰዱ ሲሆን ፤ዋና አላማቸዉም ከህዳሴው ግድብ ዙሪያ በተለይ በውሃ አሞላል ጋር በተያያዘ ሁሉን አቀፍ ተጽእኖ በሀገሪቱ ላይ ለመፍጠር በማሰብ እንደፈጸሙት ገልጸዋል፡፡የሳይበር ጥቃት የተሰነዘረባቸው ተቋማት አብዛኛዎቹ በድረ-ገጽ ግንባታ ሂደት ደህንነታችው ታሳቢ ያላደረጉ ተቋማት፤ በቀጣይነት የደህንነት ፍተሻ ያላደረጉ እና ከፍተኛ የሳይበር ደህንነት ተጋላጭነት የነበረባቸው መሆኑን የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ አረጋግጧል፡፡

በቀጣይም መሰል ጥቃቶች በስፋት፤ በረቀቀ መንገድ እና ከተለያዩ ስፍራ ሊሰነዘር እንደሚችል ግምት ውስጥ በማስገባት ግለሰቦችም ሆኑ ተቋማት ከመጠቀማቸው በፊት የድረ-ገጻቸውን ደህንነት አረጋግጠው እንዲጠቀሙ፤ ራሳቸውን ከሳይበር ደህንነት ተጋላጭነት ለመከላከል እና አስፈላጊውን የጥንቃቄ እርምጃዎችን መውሰድ እንደሚኖርባቸው ኤጀንሲው አሳስቧል።

Related Articles

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Back to top button