Uncategorized

የአፋር ክልል አሚበራ ወረዳ ከትናንት ሌሊት ጀምሮ የተከሰተው ጎርፍ

አዲስ አበባ፣ነሐሴ 28፣ 2012 በአፋር ክልል አሚበራ ወረዳ ከትናንት ሌሊት ጀምሮ የተከሰተው ጎርፍ ተከትሉ በውሃ የተከበቡ ሰዎችን ለማውጣት በሄሊኮፕተር የታገዘ ጥረት እየተደረገ መሆኑን የክልሉ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት አስታወቀ። በክልሉ የተለያዩ ወረዳዎች ቀደም ሲልም ተከስቶ በነበረው ጎርፍ የተጉዱ ወገኖች
ለመደገፍ ሲሰራ ቆይቷል። በጽህፈት ቤቱ የቅድመ-ማስጠንቀቂያና ምላሽ ዳይሬክተር አቶ አይዳሂስ ያሲን እንደገለጹት በክልሉ መካከለኛው አዋሽ የቆቃ ግድብ ሞልቶ የተለቀቀ ውሃ በአሚበራ ወረዳ የተለያዩ
ቀበሌዎች ጎርፍ አስከትሏል።

ጎርፉ በሰው ህይወት ላይ ጉዳት ባያደረስም በውሃ የተከበቡ ሰዎችን ለመታደግ በሄሊኮፕተርና  ጀልባ በመታገዝ ከአካባቢው ለማውጣት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል። ጎርፉ በእንስሳትና እርሻ መሬት ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል ብለዋል። በውሃ ለተከበቡና  ለተፈናቀሉ  ሰዎች አስቸኳይ ሰብአዊ ድጋፍ ለማድረስና የጉዳቱን መጠን ለመለየት  እየተሰራ መሆኑን ዳይሬክተሩ አሰታውቀዋል።

የአሚበራ ወረዳ የአርብቶ አደርና ግብርና ልማት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሀሰን ዲኒ እንዳሉት በወረዳው ከትናንት ማታ አራት ሰዓት ተኩል ጀምሮ በሰባት ቀበሌዎች ጎርፍ ተከስቷል። ጎርፉ ከባድ በመሆኑ  የከፋ ጉዳት ከማድረሱ በፊት በውሃ የተከበቡ  ነዋሪዎችን በማውጣት በሌላ አካባቢ ለማስፈር  በሄሊኮፕተር የታገዘ ጥረት  እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል።
ለተጎጂዎቹ የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ ለማድረስ   እየተሰራ ነው ብለዋል።

Related Articles

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Back to top button