Africa

በትግራይ ክልል ያለው ችግር የኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ነው – የደቡብ ሱዳን ምክትል ፕሬዚዳንት

አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 18፣2013  በትግራይ ክልል ያለው ችግር የኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ በመሆኑ መንግሥታቸው ጣልቃ የመግባት አጀንዳን እንደማይደግፍ የደቡብ ሱዳን ምክትል ፕሬዚዳንት ገለጹ፡፡ በደበብ ሱዳን የኢትዮጵያ አምባሳደር ነቢል ማህዲ ከደቡብ ሱዳን ምክትል ፕሬዚዳንትና የአገልግሎት ዘርፍ ክላስተር አስተባባሪ ከሆኑት ሁሴን አብዱል ባጊ አኮል ጋር በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታና በደቡብ ሱዳን የሰላም ስምምነት አፈጻጸም ዙሪያ መክረዋል።

አምባሳደር ነቢል የሁለቱ ሃገራት ግንኙነት በጠንካራ መሠረት ላይ የተገነባ መሆኑን በማውሳት ይህንን ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ በተጨባጭ የጋራ የልማት ፕሮጀክቶች መደገፍ እንደሚገባ ገልጸዋል። ከዚህ አንጻር ሃገራቱን በመንገድና በኤሌክትሪክ ኃይል መሠረተ-ልማት ለማስተሳሰር የተጀመረው ጥረት
ማሳካት ተገቢ ነው ብለዋል። የደቡብ ሱዳን የሰላም ስምምነት አተገባበር ሂደት በአጠቃላይ ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴዎች እንደሚታዩ በመግለጽ እያጋጠሙ ያሉ እንቅፋቶችን በቶሎ በመቅረፍ በሃገሪቱ አስተማማኝ መረጋጋት መፍጠር እንደሚቻል ገልጸዋል።

ከዚህ አንጻር ኢትዮጵያ እስካሁን ስታደርግ የነበረውን ድጋፍ አጠናክራ እንደምትቀጥል አረጋግጠዋል። በተጨማሪ አምባሳደሩ በሕዳሴ ግድብ ድርድር ሂደት፣ በትግራይ ክልል ወቅታዊ ሁኔታና የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሐ-ግብርን በተመለከተ ለምክትል ፕሬዚዳንቱ ገለጻ አድርገዋል። ምክትል ፕሬዚዳንት ሁሴን አብዱል ባጊ በበኩላቸው÷ ኢትዮጵያዊያን ለደቡብ ሱዳን ነጻነት ከደቡብ ሱዳናዊያን ጎን በመሰለፍ የሕይወት መስዋዕትነት የከፈሉበት መሆኑን በማውሳት ግንኙነቱ ከጥቅም ትስስር የላቀ ነው ብለዋል። በዚህ የተነሳ የደቡብ ሱዳን አመራሮች ለኢትዮጵያ የተለየ ክብር ያላቸው መሆኑን ገልጸዋል።

ይህንን ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር ሃገራቱን የበለጠ በመሠረተ-ልማት ማስተሳሰር ጊዜ ሊሰጠው እንደማይገባ ተናግረዋል። ምክትል ፕሬዚዳንቱ የሕዳሴ ግድብ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለደቡብ ሱዳንና ለአካባቢው ትልቅ ጸጋ መሆኑን በመግለጽ ልዩነቶች በውይይት ብቻ መፍታት እንደሚገባ መግለጻቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

Related Articles

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Back to top button