Ethiopia

ተሸከርካሪን በመጠቀም የሚፈፀም የቅሚያ ወንጀል ‹‹ሿሿ›› መበራከት

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 18፣ 2014 በአዲስ አበባ የሌብነት ወንጀል በየጊዜው እየጨመረ መምጣቱን ፖሊስ አስታወቀ:: በአዲስ አበባ ለህዝብ ስጋት ከሆኑ ከባድ ወንጀሎች መካከል በተለያየ መንገድ የሚፈፀም የሌብነት ወንጀል በየጊዜው እየጨመረ መምጣቱን የአዲስ አበባ ፖሊስ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ኮማንደር ፋሲካ ፋንታ ተናግረዋል። ከእነዚህ ከባድ ወንጀሎች ውስጥ ተሸከርካሪ በመጠቀም የሚፈፀም የቅሚያ ወንጀል፣ በተለምዶ ‹‹ሿሿ›› የሚባለው መኪና ውስጥ የሚፈፀም ወንጀል፣ የመኪና እና የመኪና ዕቃ ስርቆት ይጠቀሳል ብለዋል።


ነገር ግን ባለፉት 9 ወራት ከሰው መግደል እስከ ኪስ ስርቆት ያሉ ለህዝብ ስጋት የሆኑ አብዛኛዎቹ ከባድ ወንጀሎች 10 በመቶ ቀንሰዋል ብለዋል ኮማንደር ፋሲካ።
ከእነዚህም መካከል በጦር መሳሪያ የተደገፈ ዘረፋ እና ሰው መግደል በከፍተኛ ቁጥር እየቀነሰ መምጣቱን ተናግረዋል። ህዝቡ ቀንም ሌሊትም አካባቢውን በመጠበቅ፣ ለፖሊስ መረጃ በመስጠት እና የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ ከፍተኛ ተሳትፎ ማድረጉ እነዚህን ወንጀሎች በመከላከልና በመቆጣጠር ረገድ ትልቅ ውጤት
እንዲመጣ አግዟል ብለዋል ዳይሬክተሩ፡፡


ባለፉት 9 ወራት 8 ሺህ 211 የተፈፀሙ ከባድ ወንጀሎች የተመዘገቡ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ 61 በመቶ የተመዘገቡ ከባድ ወንጀሎች ተጠርጣሪዎቹ መያዛቸውን ተነግሯል። ከእነዚህ ወንጀሎች ውስጥ አንዳንዶቹ በምርመራ ላይ ያሉ ሲሆኑ፣ ቀሪዎቹ ደግሞ በፍርድ ሂደት ላይ ያሉ እና የፍርድ ውሳኔ የተሰጠባቸው እንደሆኑ ዳይሬክተሩ ገልጸዋል። ባለፉት 9 ወራት ከተመዘገቡ መካከለኛ ወንጀሎች እና ቀላል ወንጀሎች በቅደም ተከተል 56 በመቶ እና 90 በመቶ በቁጥጥር ስር ማዋል መቻሉን ፖሊስ ጠቁሟል። በዚህ ወቅት በመዲናዋ ለህዝብ ስጋት ናቸው የሚባሉ ከባድ ወንጀሎችን በ15 በመቶ ለመቀነስ ታቅዶ 10 በመቶ መቀነስ መቻሉንም ኢቢሲ ዘግቧል፡፡

Related Articles

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Back to top button