Ethiopia

የአዲስ አበባ የትራንስፖርት ቢሮ ለአሽከርካሪዎች የሰጠው ማስጠንቀቂያ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 2፣ 2014 የትራንስፖርት አገልግሎቱን በሚያስተጓጉሉ የህዝብ ትራንስፖርት ሰጪ አሽከርካሪዎች ላይ እርምጃ እወስዳለሁ ሲል የአዲስ አበባ የትራንስፖርት ቢሮ አስጠነቀቀ::
የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር እጸገነት አበበ ለኢቢሲ እንደገለጹት፣ ማንኛውም የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች፣ ሸገር የብዙሃን ትራንስፖርት ድጋፍ ሰጪዎችን ጨምሮ በተመደቡበት የስምሪት መስመር በመገኘት በተቀመጠው የታሪፍ መጠን ብቻ አገልግሎቱን መስጠት ይገባቸዋል፡፡


በጥናት መመለስ የሚገባቸው ጉዳዮች ካሉም ቢሮው አሰራሩን በመፈተሽ በሂደት ምላሽ እሰጣለሁ ብሏል፡፡ በሸገር የብዙሃን ትራንስፖርት አገልግሎት በኪራይ ውል አገልግሎት የሚሰጡ ድጋፍ ሰጪዎች ከቢሮው ጋር በገቡት ውል መሠረት የትራንስፖርት አገልግሎት የማይሰጡትን ቢሮው ከስምምነት ውል ውጪ እንደሚያደርጋቸው አውቀው ወደ ነበሩበት መስመር በፍጥነት እንዲገቡና ስራቸውን እንዲሰሩም ቢሮው ጥሪ አስተላልፏል፡፡


ከነዳጅ ዋጋ ጭማሪ ጋር ተያይዞ ህብረተሰቡን ከታሪፍ በላይ በሚያስከፍሉ፣ መስመር በሚያቆራርጡ፣ የመስመር ታፔላ በማይሰቅሉ /ከእይታ ውጪ በሚያደርጉ/፣ ታሪፍ በማይሰቅሉ /በማይለጥፉ/፣ አሽከርካሪዎችን ከተፈቀደላቸው አገልግሎት ውጪ የሚያውሉ የህዝብ ትራንስፖርት ሰጪ አሽከርካሪዎች ካሉ ከወዲሁ ጥብቅ ጥንቃቄ በማድረግ ስራቸውን በተገቢው መንገድ እንዲሰሩና ማህበረሰቡን እንዲያገለግሉ ጠይቋል፡፡ ቢሮው ህግና መመሪያዎችን ተከትለው በማይሰሩ የህዝብ የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ አሽከርካሪዎች ላይ የማያዳግም እርምጃ እንደሚወስድ ነው ያስታወቀው፡፡ ህብረተሰቡ ላላስፈላጊ ወጪና እንግልት እንዳይዳረግ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር እንደሚሰራ ቢሮው አስታውቋል፡፡

Related Articles

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Back to top button