EthiopiaPoliticsRegionsSocial

ፖሊስ ጦላይ ወታደራዊ ማሰልጠኛ የሚገኙ የአዲስ አበባ ወጣቶች በመጪው ሃሙስ ወደየቤታቸው ይመለሳሉ አለ

አርትስ 06/02/2011
የአዲስ አበባ ፖሊስ በጎዳና ላይ ንብረት ሲያወድሙና ሁከት ሲፈጥሩ ነበር በማለት በቁጥጥር ስር ያዋላቸውንና ጦላይ ወታደራዊ ማሰልጠኛ የሚገኙ 1174 ወጣቶችን በመጪው ሃሙስ እንደሚለቃቸው አስታውቋል።
ወጣቶቹ ወደማሰልጠኛው የተላኩት የተሃድሶ ስልጠና እንዲወስዱ መሆኑን ፖሊስ ይገልጻል።
የፖሊስ ኮሚሽኑ የህዝብ ግንኙነት መምሪያ ሃላፊ ኮማንደር ፋሲካ ፈንታ ለአርትስ ቲቪ እንዳስታወቁት ወጣቶቹ በቆይታቸው የህገመንግስት ስልጠና የተከታተሉ ሲሆን በሁከት እና ግጭት ውስጥ መሳተፋቸው ጥፋት መሆኑንም በራሳቸው ተነሳሽነት አምነዋል።
እንደኮማንደር ፋሲካ ገለጻ ሁከት እና ግርግር ውስጥ ገብተው ጥፋት ላይ በመሳተፋቸው በቁጥጥር ስር ከዋሉት ወጣቶች ውስጥ ከዚህ ቀደም በፖሊስ የተመዘገበ የወንጀል ሪከርድ ያለባቸውም ይገኙበታል።
ኮማንደሩ እንደሚሉት ወጣቶቹ ወደማሰልጠኛ ጣቢያው የተላኩት ስለሰላም እና ህጋዊ ስርዓት እንዲሁም የሃገሪቱን ህገመንግስት በተመለከተ ስልጠና እንዲወስዱ ሆኖ ሳለ ታስረው እየተቀጡ እንደሆነና ከመካከላቸውም የሞቱ እንዳሉ ተደርጎ በማህበራዊ ሚዲያ የሚራገበው መረጃ ግን ከእውነት የራቀ ነው ።
ሁሉም ወጣቶች በመጪው ሳምንት ስልጠናቸውን አጠናቀው ወደየቤታቸው እንደሚመለሱ የተናገሩት ኮማንደር ፋሲካ የወጣቶቹ አያያዝ እና ቆይታ ምን መልክ እንደነበረው የሚያረጋግጥና ወጣቶቹን አነጋግሮ ትክክለኛውን መረጃ ለህዝብ የሚያደርስ የሚዲያ ቡድን ወደስፍራው መላኩንም ጨምረው ገልጸዋል።

Related Articles

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Back to top button