በአራት ኪሎ እሪ በከንቱ አካባቢ በግንባታ ላይ ያለ ህንፃ ተደርምሶ 6 ሰዎች ቆሰሉ
አርትስ 12/02/2011
ነገሩ እንዲህ ነው አራዳ ክፍለ ከተማ ልዩ ስሙ እሪ በከንቱ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የፌደራል ኮሚዮኒኬሽን ፅህፈት ቤት የሚያስገነባዉ ህንፃ አራተኛ ወለል ደርሷል፤ አርማታም ተሞልቷል፡፡
በትላንትናዉም ዕለት ግንባታውን የሚያከናውኑ ሁሉም ሰራተኞች በስራ ገበታቸው ተገኝተዋል፡፡ ከ ቀኑ 7 ሰዓት ሲሆን ግን ያላሰቡት ያልጠበቁት አደጋ ገጠማቸው፡፡
አርማታው ተሞልቶ ቀጣይ ስራ የሚጠብቀው ህንፃ ባልታወቀ ምክንያት ተደርምሶ 6 ሰዎች ከባድ እና ቀላል ጉዳት ሲደርስባቸው 15 ሰራተኞች ደግሞ ያገኙት ነገር ላይ ተንጠልጥለው ለመትረፍ ችለዋል፡፡ ተጎጂዎቹም ጥቁር አንበሳ እና ጋንዲ ሆስፒታል ህክምና እየተደረገላቸው ይገኛል፡፡
የእሳት እና ድንገተኛ አደጋዎች መከላከል እና መቆጣጠር በለስልጣን የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ንጋቱ ማሞ ለአርትስ ቲቪ እንደተናገሩት መንስኤው እየተጣራ ነው፡፡
ኃላፊው በተጨማሪ ባሳለፍነው በ2010 ዓ.ም ብቻ በኮንስትራክሽን ዘርፍ በደረሰ ድንገተኛ አደጋ ምክንያት 10 ሰዎች የሞቱ ሲሆን 53 ሰዎች ላይ ደግሞ ከባድ እና ቀላል ጉዳት ደርሷል በማለት ገልፀዋል፡፡
የኮንስትራክሽን ህግ እና መመሪያ ጠብቆ አለመስራት ፤ ሰራተኛው ለስራ የሚመጥን አለባበስ ወይም የጉዳት መከላከያ (ሴፍቲ) አለመጠቀም ዋንኛ ምክንያቶች እንደሆኑ አሰረድተዋል፡፡
ለዚህም ችግር የሚመለከተው አካል ኃላፊነቱን ወስዶ መጠየቅ አለበት ሲሉ ተናግረዋል፡፡