አቶ በረከትና አቶ ታደሰ በሙስና መጠርጠራቸው ፖለቲካዊ ነው ብለው እንደሚያምኑ አቶ ጌታቸው ረዳ ተናገሩ
አቶ በረከትና አቶ ታደሰ በሙስና መጠርጠራቸው ፖለቲካዊ ነው ብለው እንደሚያምኑ አቶ ጌታቸው ረዳ ተናገሩ
በሁለቱ ግለሰቦች መያዝ ላይ አስተያየታቸውን የተጠየቁት የቀድሞው የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ጽህፈት ቤት ሚንስትር አቶ ጌታቸው ረዳ እስሩ ላይ ጥርጣሬ እንዳለቸውና ፖለቲካዊ ነው ብለው እንደሚያምኑ ለቢቢሲ አማርኛ ተናግረዋል።
የቀድሞው ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣን አቶ በረከት ስምኦንና አቶ ታደሰ ካሳ በሙስና ተጠርጥረው በቁጥጥር መዋላቸው እንዳስደነቃቸውና በዚህ ደረጃ ያልጠበቁት መሆኑን አቶ ጌታቸው ረዳ ተናግረዋል።
ለእስሩ ሌላ ምክንያት ካለ በግልጽ እንዲነገር የጠየቁት አቶ ጌታቸው ከሙስና አንጻር የሚጠየቁ ከሆነ አቶ በረከትና አቶ ታደሰ በመጨረሻው ደረጃ ላይ የሚገኙ ናቸው ብለው እንደሚያምኑ ገልጸዋል።
“እንደ ፓርቲው ከፍተኛ አመራር እርምጃው አስደንቆኛል። ከሙስና ጋር በተያያዘ ስማቸው የሚነሳ በርካታ ሰዎች አሉ፤ መናገር የምፈልገው በረከትና ታደሰ ግን ከዚህ አንጻር በመጨረሻው ደረጃ ላይ ሊቀመጡ የሚችሉ ናቸው። ነገር ግን ስለማንም በእርግጠኝነት መናገር አልችልም” ብለዋል፡፡
ለእራሳቸው ይሰጉ እንደሆነ የተጠየቁት አቶ ጌታቸው በግላቸው ምንም ስጋት እንደሌላቸው ነገር ግን በእሳቸው ላይ የተቀነባበረ ክስ ቢቀርብባቸው ብዙም እንደማይደንቃቸው ተናግረዋል።
ጨምረውም ቢሆንም አመራሩ ይህን ያህል ይወርዳል ብለው ስለማያስቡ “ጠቅላይ ሚኒስትሩ ነገሮችን ያስተካክላሉ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ” ብለዋል።
አንድ ሰው የፖለቲካ እንቅስቃሴ የሚያደርግ ወይም የክልል ወይም የፌደራል መንግሥትን የሚተች በመሆኑ ለእስር የሚዳረግ ከሆነ፤ ተገቢውን ፍትህ ያገኛል ብሎ መጠበቅ በእኔ በኩል የዋህነት ነው። ቢሆንም ተገቢውን ፍትህ ያገኛሉ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ” ብለዋል።
አቶ በረከት ስምኦን እና አቶ ታደሰ ካሳ ትናንት አዲስ አበባ ከሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው በቁጥጥር ስር መዋላቸውንና በክልሉ ፍርድ ቤት ስለሚዳኙ ወደ ባህር ዳር መወሰዳቸውን የአማራ ጸረ ሙስና ኮሚሽን አስታውቋል።