የበረራ አስተናጋጇ ከአውሮፕላን ላይ ወደቀች
አርትስ 15/02/2011
አደጋ በየትኛውም ቦታና ሁኔታ የሚያጋጥም ቢሆንም የበረራ አስተናጋጇ በር ልትዘጋ ስትል ከአውሮፕላን ላይ ወደቀች የሚል ዜና ግን ጆሮ የለመደው አይነት አይደለም።
ህንድ ውስጥ የተሰማው ዜና ግን ይህ ነው። ሙምባይ አውሮፕላን ማረፊያ ውስጥ ንብረትነቱ የኤየር ኢንዲያ የሆነ ቦይንግ ትሪፕል ሰቨን የሚባል ግዙፍ አውሮፕላን ተሳፋሪ ጭኖ ለመብረር እየተዘጋጀ ነው።
የበረራ አስተናጋጇ አውሮፕላን ውስጥ የነበሩትን ተሳፋሪዎች እንኳን ደህና መጣችሁ ለማለት በዝግጅት ላይ ከነበሩት ባልደረቦቿ ጋር ጣደፍ ጣደፍ እያለች ወደኋላ በር ሄደች።ከዚያም በሩን ለመዝጋት ዘወር አለች። ከዚያ በኋላ ባልደረቦቿም ይሁን ተሳፋሪዎቹ አውሮፕላኑ ውስጥ አላዩዋትም። ከዚያ ግዙፍ አውሮፕላን ላይ ወደቀች።
በዚህች የበረራ አስተናጋጅ ላይ የደረሰባት ይኸው አደጋ ለእግር ስብራት ዳርጓታል።በጊዜው ራሷን እንዳልሳተች ግን ከባድ ጉዳት ላይ እንደነበረች ተነግሯል ።
የአየርመንገዱ ሃላፊ ፕራቪን ባትናጋር ለፈረንሳይ ዜና ወኪል እንደተናገሩት በዚህች የ52 ዓመት እድሜ ባላት የበረራ አስተናጋጅ ላይ የደረሰውን አደጋ ትክክለኛ ምክንያት ለማወቅ ምርመራ እየተካሄደ ነው።