የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ በአዲስ አበባ በ43 ሚሊዮን ብር ወጪ የደህንነት ካሜራዎችን እየገጠምኩ ነው አለ
የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ በአዲስ አበባ በ43 ሚሊዮን ብር ወጪ የደህንነት ካሜራዎችን እየገጠምኩ ነው አለ፡፡
በመዲናዋ ከቀይ ሽብር ሰማዕታት ሀውልት እስከ ቦሌ አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ አደባባይ ቁጥራቸው 140 የሆኑ የደህንነት ካሜራዎች መገጠማቸው ተነግሯል፡፡
በኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ የኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ አብዱልባሲጥ አህመድ፣ የመጀመሪያው ዙር የከተማዋ የደህንነት ካሜራ ገጠማና ስራ 90 በመቶ ተጠናቋል ብለዋል።
ገጠማቸው ተጠናቆ በሙከራ ላይ ይገኛሉ የተባሉት ካሜራዎችም በጥቂት ወራት ውስጥ ሙሉ በሙሉ አገልግሎት የሚጀምሩ መሆኑን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።
ይህ ፕሮጀክት ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ሲጀምር ፖሊስ በከተማዋ ወንጀልን ለመቀነስ የሚያደርገውን ጥረት ያግዛል ተብሏል።
በፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን የአይሲቲ መሰረተ ልማት ዝርጋታ ዲቪዥን ሀላፊ ምክትል ኢንስፔክተር አንድነት ሲሳይ በበኩላቸው ፥ ቴክኖሎጂው ባደጉት ሀገራት በሰፊው በስራ ላይ የሚውል ነው ብለዋል፡፡
ኢንስፔክተሩ ቴክኖሎጂው በተለይ ወንጀልን ቀድሞ ከመከላከል አንጻር ያለው ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑንም ገልፀዋል።