ፕሬዝዳንት ፖልካ ጋሜ በሺህ ከሚቆጠሩ የሀገሪቱ ዜጎች ጋር ከመኪና ነፃ ቀን አከበሩ
አርትስ 12/02/2011
የሩዋንዳው ፕሬዚዳንት ፖልካ ጋሜ ‹ከመኪና ነፃ› በሚል መሪ ሐሳብ የሚከበረውን የአረንጓዴ ልማት ማበረታቻ ዝግጅት በኪጋሊ በሺዎች ከሚቆጠሩ ዜጎች ጋር አክብረዋል፡፡
እንደ አውሮፓዊያኑ አቆጣጠር በ2016 በመዲናዋ ኪጋሊ መኪና እንዳይሽከረከር በማገድ በየአመቱ ‹‹ከመኪና ነፃ›› ቀን እንዲከበር የታወጀ ሲሆን ሩዋንዳ ቀኑን ስታውጅ ከካርቦን ልቀት ነፃ የሆነ አካባቢን ለመፍጠር እና ሰዎች ከነዳጅ ውጭ ያሉ የተሸከርካሪ አማራጮችን እንዲጠቀሙ ለማበረታታት ታስቦ ነበር፡፡
ሲጂቲኤን እንደዘገበው ‹ከመኪና ነፃ› ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃም በየዓመቱ መስከረም 12 ቀን ተከብሮ ይውላል፡፡ በዕለቱም በተለይም በከተሞች መኪና እንዳይሽከረከር በማድረግ ሰዎች በእግራቸው እና ሌሎች ከነዳጅ ነፃ የሆኑ የትራንስፖርት አማራጮችን እንዲጠቀሙ ይደረጋል፡፡
በአካባቢው የአየር ንብረት ለውጥ ከፍተኛ መሻሻሎችን ያስመዘገበችው ሩዋንዳ እንደ ኬንያ ላሉ ሌሎች የአፍሪካ ሀገሮች እንደምሳሌ መጠቀሷ ይታወሳል፡፡