loading
የኦጋዴን ብሄራዊ ነፃ አውጪ ግንባር (ኦብነግ) ልኡክ ዛሬ ማምሻውን አዲስ አበባ ገብቷል።

በግንባሩ ቃል አቀባይ አቶ አዳኒ አብዱልቃድር ሄርሞጌ የተመራው እና 3 አባላትን ያለው ልኡኩ ዛሬ ማምሻውን አዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርስ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ሚኒስትር ደኤታ አቶ ካሳሁን ጎፌ አቀባበል አድርገዋል።

ወደ ሀገር የገባውን ልኡክ የመሩት አቶ አዳኒ አብዱልቃድር ሄርሞጌ፥ ግንባሩ ወደ ሀገር ቤት ለመግባት የወሰነው የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ጥሪን ተከትሎ መሆኑን አስታውቀዋል።

እንዲሁም በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ያለውን ሁኔታ ለማረጋጋት ታስቦ በዚህ ፍጥነት ወደ ሀገር መግባታቸውንም ቃል አቀባዩ ተናግረዋል።

ኦብነግ ከዛሬ ጀምሮ የተኩስ አቁም ማወጁን የተናገሩት አቶ አዳኒ፥ ይህም በቀጠናው
ምንም አይነት የጥይት ድምጽ እንዳይሰማ ስለሚፈልግ እና ክልሉን ለማረጋጋት መሆኑንም አስታውቀዋል።

እንዲሁም የኢትዮጵያ መንግስት የሰብአዊ መብትን ለመጠበቅ በርካታ ስራዎችን ሰርቷል ያሉት ቃል አቀባዩ፥ ኦብነግም ይህንን ከግምት ውስጥ በማስገባት ወደ ሀገር ገብቶ በሰላማዊ መንገድ ለመታገል መወሰኑን ገልፀዋል።

ለግንባሩ ልኡክ አቀባበል ያደረጉት የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ሚኒስትር ደኤታ አቶ ካሳሁን ጎፌ በበኩላቸው፥ መንግስት ባደረገው ጥሪ መሰረት በርካታ የፖለቲካ ሀይሎች ወደ ሀገር ቤት መግባታቸውን ጠቅሰዋል።

መንግስትም እነዚህ የፖለቲካ ሀይሎችን ለሚያደናቅፉ አሰራሮች መፍትሄ በመስጠት እና አማራጮችን በማስፋት ራሳቸውን ለምርጫ እንዲያዘጋጁ ድጋፍ ያደርጋልም ብለዋል።

የኦጋዴን ብሄራዊ ነፃ አውጪ ግንባር (ኦብነግ) በዛሬው እለት ባወጣው መግለጫ የተናጠል የተኩስ አቁም ማወጁ ይታወሳል።

ኦብነግ የተናጥል የተኩስ ቁም ውሳኔ ላይ የደረሰውም የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ያቀረቡትን ጥሪ ተከትሎ እንደሆነም ግንባሩ በመግለጫው አስታውቋል።

የኢትዮያ መንግስትም የተጀመረው የሰላም ሂደት ግቡን እስኪመታ በግንባሩ ላይ ላይ የሚካሄዱ ወታደራዊ ይሁን ሌሎች እርምጃዎችን እንዲያቂምም ጥሪውን አቅርቧል።

የኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሰኔ 28 2010 ዓ.ም ባካሄደው ስብሰባው የኦጋዴን ብሄራዊ ነፃ አውጪ ግንባር (ኦብነግ) የሽብርተኝነት ፍረጃ ማንሳቱ ይታወሳል።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ2003 ዓ.ም ነበር ኦነግ፣ ኦብነግና ግንቦት 7 እንዲሁም ከሀገር ውጪ አልቃይዳና አልሸባብን ጨምሮ አሸባሪ ድርጅቶች ብሎ የፈረጀው።
ኤፍ.ቢ.ሲ

Write a Reply or Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *