EthiopiaPoliticsRegionsSocial

የድሬዳዋ ፖሊስ ለ13 ሰዎች ህልፈትና ለንብረት መውደም ምክንያት የሆነውን ግጭት የምርመራ ውጤት ይፋ አደረገ

አርትስ 15/1/2011
የድሬዳዋ አስተዳደር ፖሊስ ኮሚሽን ሐምሌ 29 2010 ዓ.ም ለ13 ሰዎች ህልፈትና ለንብረት መውደም ምክንያት በሆነው ግጭት ላይ ሲያካሂድ የነበረውን የምርመራ ውጤት ዛሬ ይፋ አድርጓል።

ኮሚሽኑ ዛሬ ጉዳዩን አስመልክቶ በሰጠው መግለጫ፥ በእለቱ በተፈጠረው ሁከት በ3 መኖሪያ ቤቶች ውስጥ የነበሩ የ13 ንፁሀን ዜጎች ህይወት ማለፋንና በ42 ቤቶች ላይ ቃጠሎና ዝርፊያ መካሔዱን ገልጿል።

ኮሚሽኑ ባደረገው ምርመራ 4 ግለሰቦች በቤት ቃጠሎ፣ 21 ግለሰቦች ደግሞ በቀጥታ በግድያው መሳተፋቸውን በማስረጃ ማረጋገጡን ገልጾ በ5 ተጠርጣሪዎች ላይ ማስረጃ እያሰባሰበ መሆኑን በመግለጫው አስረድቷል።

ከ13 ሟቾች 8ቱ የ1 ዓመት ህፃንን ጨምሮ ከ15 ዓመት በታች እድሜ ያላቸው ሲሆኑ፥ በንብረት ረገድም ከ6 ሚሊየን ብር በላይ ግምት ያለው ንብረት ላይ ጉዳት መድረሱ ተገልጿል።

በግጭቱ ወቀት ግድያ ፣የቤት ቃጠሎና የዝርፊያ ተደራራቢ ወንጀል በመፈፀሙ ምርመራውን ለማጠናቀቅ ጊዜ መውሰዱን በመግለጫው ተመልክቷል።

የተፈጠረውን ግጭት የብሔር ግጭት ለማስመሰል ሙከራ መደረጉን፣ የድሬዳዋ ሕዝብ ያዳበረው የአብሮ መኖር እሴት ለእንዲህ አይነቱ ኋላ ቀር አስተሳሰብ የማይመች በመሆኑና ፖሊስ ሁኔታውን መቆጣጠር በመቻሉ የታሰበው ሊሳካ አለመቻሉን የድሬዳዋ ፖሊስ ኮሚሽን ሕዝብ ግኑኝነት ዲቪዥን ሀላፊ ዋና ሳጅን ባንታለም ግርማ ገልፀዋል።

ከሀምሌ 29 2010 ዓ.ም በኋላ ነሀሴ 29 2010 ዓም በድጋሚ ግጭት ለማስነሳት መሞከሩን የገለጹት ዋና ሳጂን ባንታለም ግርማ፥ ፖሊስ ጉዳት ከመድረሱ በፊት ሁኔታውን በመቆጣጠር 300 የሚሆኑ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር ማዋሉንም አስረድተዋል።

ከተያዙት ውስጥ በ77ቱ ላይ ምርመራ አጣርቶ ለአቃቤ ህግ በመላኩ አቃቤ ህግ በፍርድ ቤት ክስ መመስረቱን ተናግረዋል።

ሰሞኑን በቤቶች ላይ የተደረገውን ምልክት በተመለከተም ፖሊስ ከህብረተሰቡ ተባብሮ በመስራቱ ምልክቱ ወደ ተግባር እንዳይለወጥ መደረጉን የህዝብ ግኑኝነት ሀላፊው ገልፀዋል።

ዋና ሳጅን ባንታለም ግርማ አክለውም፥ ከነገ ጀምሮ በክርስትና እምነት ተከታዮች የሚከበረው የደመራና የመስቀል በአል ሀይማኖታዊ እሴቱን ጠብቆ በሰላም እንዲከበር ፖሊስ አስፈላጊውን ዝግጅት ማጠናቀቁንም ገልፀዋል።

ሰላም ወዳዱ የድሬዳዋ ሕዝብም ከስሜታዊነት ርቆ እንደ ሁልጊዜው ከፖሊስ ጋር በመተበባር ለሰላሙ ዘብ እንዲቆም ጥሪ አቅርበዋል።

ኮሚሽኑ ህብረተሰቡ በተለይም ወጣቶች እንዲሁም የአስተዳደሩ አመራሮች ሁከትን ለማክሸፍና ሠላምን ለማረጋገጥ ላሳዩት ቁርጠኝነት ምስጋና ማቅረባቸውን የድሬደዋ ከተማ ከንቲ ጽህፈት ቤት አስታውቋል።
ኤፍ.ቢ.ሲ

Related Articles

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Back to top button