EthiopiaPoliticsRegionsSocial

እያንዳንዱ ወቅትና ዘመን “አርበኝነትን” ይጠይቃል፤ ለዚህ ትውልድ የ”አርበኝነት” ብያኔ ድህነትን ከልብ መጠየፍ እና በልማት ድል መንሳት ነው አሉ ም/ጠ/ሚ/ር እና የብአዴን ሊቀመንበር አቶ ደመቀ መኮንን። ብአዴን 12ተኛ ድርጅታዊ ጉባኤውን ጀምሯል።

አርትስ 17/01/2011
እያንዳንዱ ወቅትና ዘመን “አርበኝነትን” ይጠይቃል፤ ለዚህ ትውልድ የ”አርበኝነት” ብያኔ ድህነትን ከልብ መጠየፍ እና በልማት ድል መንሳት ነው፡፡ በዚህ የለውጥ ዘመን አርበኝነት ጥላቻን በፍቅር፤ ቂም-በቀልን በይቅርታ፤ መከፋፈልና መናቆርን በመቻቻልና በመደመር መሻገር ነው፡፡ ብለዋል አቶ ደመቀ።

እኛ የዛሬዎቹ ትውልድ ባለቤቶች፣ ለቀጣዩ ትውልድ የምናወርሳት ሀገር፣ ለዜጎቿ የተመቸችና የበለፀገች ትሆን ዘንድ ይህንን የአርበኝነት ታሪካችንን የምናሳየው ከድህነት እና ኋላቀርነት ጋር በምናደርገው ፍልሚያ ነው፡፡

ሀገርን መውደድ እና ማንነትን ማክበር፤ ድህነትን አዝሎ ግንጥል ጌጥ ነው፡፡ የድህነትና የኋላቀርነት ባሪያ ሆኖ ነፃነት የለም፡፡ አሁን የደረስንበት ምዕራፍ ብዙ ተጉዘን የመጣንበት ቀጥሎም ረጅም ጉዞ የሚጠይቀን ወሳኝ ወቅት ነው፡፡ ከፖለቲካው አንፃር ዛሬም ሀገራችን በሁለት ፅንፈኛ ሀይሎች መካከል በተወጠረ ፖለቲካ ውስጥ ትገኛለች፡፡ ክልላችንም የዚህ ዓይነተኛ መገለጫ ሆኖ ይታያል፡፡

በአንድ በኩል ሁሉን የደፈጠጠና የጨፈለቀ ልሙጥ ሀገራዊ ማንነትን ብቻ አንግቦ የተነሳ ጠቅላይና አሃዳዊ አመለካከት የኢትዮጵያን መልከ-ብዙ ዕውነታ በካደ ደረጃ ፅንፍ ይዞ እየተራገበ ይገኛል፡፡

በሌላ በኩል ብሄረሰባዊ ማንነትን ከሌሎች መነጠያና ማግለያ ያደረገ እና ፅንፈኛ ብሄርተኝነት በሚቀነቀንበት ወቅት ላይ እንገኛለን፡፡

የአማራ ህዝብ ሁሉን ደፍጣጩን እና ጨፍላቂውን ልሙጥ ማንነት እንዲሁም ከሌሎች የሚነጥለውንና የሚያገለውን ራስን ከልክ በላይ የሚያወድስ ማንነትን የሚሸከም ትከሻ የሌለው በእኩልነት የሚያምን ከሌሎች ጋር ወዶ እና ፈቅዶ ተሳስሮ የኖረ ህዝብ ነው ብሎ ብአዴን ያምናል፡፡

በመሆኑም ይህንን የመሰለውን መገለጫ ባለቤት የሆነውን የአማራን ህዝብ የሚመራው ድርጅታችን ብአዴን በእነዚህ ሁለት ፅንፎች መሀል ሚዛን ሆኖ የመቆም ኃላፊነቱን በብቃት መወጣት የሚጠይቀው ወሳኝ ወቅት ላይ ይገኛል ብለዋል።

መልካም አስተዳደርን ማስፈን፣ የፍትህ ጥማትን ማርካት፣ የዲሞክራሲ ምህዳሩን ማስፋት ሕዝባችን ከእኛ በአፋጣኝ እየጠየቃቸው ያሉ የለውጥ አጀንዳዎቻችን ናቸው ያሉት አቶ ደመቀ ለውጡ ድንበር የለሽ ነው፡፡ ብአዴናዊ፣ ኢህአዴጋዊ፣ ሕዝባዊ እና ሕገ-መንግስታዊ ስፋትን ይዞ ይቀጥላል ሲሉ ተናግረዋል። በመጨረሻም ይህ ታሪካዊ ጉባኤ ብአዴን በዚህ ሂደት ውስጥ የለውጡ መሪ ሆኖ የሚወጣበትን አቅጣጫ የሚያላብሱ ውሳኔዎችን ተወያያቶ እንደሚያሳልፍ፤ እንዲሁም የአስተሳሰብ አንድነት በመገንባት ለውጡን በሚጠበቀው ከፍታ የሚያስቀጥሉ እና በቅርብ በሞት እንዳጣነው እንደ ጓድ ተስፋዬ ጌታቸው ዓይነት ለእውነትና ለፍትህ በጽናት የሚቆሙ አመራሮችን እንደሚሰይም ፅኑ እምነቴ ነው ብለዋል።
12ኛው የብአዴን ድርጅታዊ ጉባኤ ብዙ ውሳኔዎችን ያስተላልፋል ተብሎ ይጠበቃል።

Related Articles

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Back to top button