loading
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት መኖሪያ ህንጻ ውስጥ ለጥበቃ ስራ ተመድቦ የነበረ አንድ የፖሊስ አባል በከፈተው ተኩስ ሁለት የፖሊስ ባልደረቦችን ገድሎ ስድስት ማቁሰሉ ተረጋግጧል።

አዲስ አበባ ውስጥ በተለምዶ ወሎ ሰፈር ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በሚገኘው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት መኖሪያ ህንጻ ውስጥ ለጥበቃ ስራ ተመድቦ የነበረ አንድ የፖሊስ አባል በከፈተው ተኩስ ሁለት የፖሊስ ባልደረቦችን ገድሎ ስድስት ማቁሰሉ ተረጋግጧል።

አርትስ 24/01/2011

በአካባቢው የደረሱ የጸጥታ ሃይሎች ግለሰቡን ለማስቆም ባደረጉት የተኩስ ልውውጥ ወንጀል ፈጻሚው መገደሉም ታውቋል።
የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ለአርትስ ቲቪ እንደገለጸው ግለሰቡ ተኩስ የከፈተው በዛሬው ዕለት ከሌሊቱ ሰባት ሰዓት ላይ ሲሆን የገደለውም ሁለት የስራ አለቆቹን ነው።
ወንጀሉን ከፈጸመ በኋላ ወደፎቁ የላይኛው ክፍል በመውጣት ላይ ሳለ በቁጥጥር ስር ሊያውሉት ሲከታተሉት የነበሩትን ስድስት የስራ ባልደረቦቹን በመተኮስ አቁስሏቸዋል።
ለጥበቃ በታጠቀው ክላሽንኮቭ ጠመንጃ ተኩሱን እንደከፈተ የተረጋገጠው ይህ የፖሊስ አባል አለቆቹን ከገደለ በኋላ ተጨማሪ መሳሪያ ከባልደረቦቹ በመቀማት ሊይዙት በመጡት የጸጥታ ሃይሎች ላይ እስከ ማለዳ ደረስ ሲተኩስ ቆይቷል።
ይኸው ግለሰብ ተጨማሪ ጥቃት ከመፈጸሙ በፊት ለማስቆም ሲሞክሩ ከነበሩት የመከላከያ ሰራዊትና የፖሊስ አባላት ጋር የተኩስ ልወውጥ በማድረጉ ከማለዳው ሁለት ሰዓት አካባቢ ሲሆን የተገደለ መሆኑ ተረጋግጧል።
የአዲስ አበባ ፖሊስ የወንጀሉን ምክንያት ለማጣራት ጥረት እያደረገ ሲሆን ባልተረጋገጠ መረጃ ግን ግለሰቡ ጥቃቱን የፈጸመው ከፖሊስ አመራሮቹ ጋር ግጭት ውስጥ በመግባቱ ነው ተብሏል።
በተኩስ ልውውጡ የቆሰሉት የፖሊስ አባላት ለህክምና ወደሆስፒታል መላካቸው ተረጋግጧል። በአሁኑ ወቅት ሁኔታዎች የተረጋጉ ሲሆን ለትራፊክ ዝግ የነበረው መንገድም ተከፍቷልብሏል ፖሊስ።
አርትስ ቲቪ ሁኔታውን በማጣራት ላይ ሲሆን አዲስ መረጃ ሲኖር እየተከታተለ ያደርሳል ።

Write a Reply or Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *