loading
የብሄራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ከማዕከላዊና ምዕራብ ጎንደር ዞኖች ለተፈናቀሉ ዜጎች ድጋፍ ማድረግ ጀምሬአለሁ አለ

የብሄራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ከማዕከላዊና ምዕራብ ጎንደር ዞኖች ለተፈናቀሉ ዜጎች ድጋፍ ማድረግ ጀምሬአለሁ አለ።

የአማራ ክልል መንግስት በበኩሉ የተደረገው ድጋፍ ከተፈናቃዮቹ ቁጥር እና ከሚፈልጉት ድጋፍ አንፃር በቂ አይደለም ብሏል፡፡

የብሄራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን በማዕከላዊ እና ምዕራብ ጎንደር ዞኖች በነበረ አለመረጋጋት  ለተፈናቀሉ ዜጎች ድጋፍ ማድረግ መጀመሩን በብሄራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን የአቅርቦትና ሎጂስቲክ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አይድሩስ ሀሰን ከአርትስ ቲቪ ጋር በነበራቸው የስልክ ምልልስ ነግረውናል፡፡

እንደ ዳይሬክተሩ ገለፃ የተፈናቃዩች ቁጥር ከ45 ሺህ በላይ ነው፡፡

በአሁኑ ሰአት በጥቅሉ በአማራ ክልል ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ከመኖሪያ ቀያቸው የተፈናቀሉ ከ90 ሺህ ባላይ  ዜጎች በጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያዎች ይገኛሉ።

ከዚህም  ውስጥ አብዛኛዎቹ በማዕከላዊና ምዕራብ ጎንደር ተፈጥሮ በነበረው የፀጥታ ችግር የተፈናቀሉ ዜጎች መሆናቸውን ሰምተናል፡፡

በአሁኑ ወቅትም ከሁለቱ ዞኖች የተፈናቀሉ ከ45 ሺህ በላይ የሚሆኑ ዜጎች በ13 ጊዜያዊ መጠለያ ካምፖች እንደሚገኙ የክልሉ መንግስት ማስታወቁ ይታወሳል፡፡

አቶ አይድሩስ ሀሰን በጎንደር እና አካባቢው መፈናቀል ሲከሰት ይህ ለሶስተኛ ዙር መሆኑን አንስተው  የብሄራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር  ኮሚሽንም በሁለቱም ዙሮች ለተፈናቀሉ ከ9 ሺህ በላይ ዜጎች  በክልሉ መንግስት ጥያቄ መሰረት የሰብአዊ እና የቁሳቁስ እርዳታ እያደረገ ነው ብለዋል፡፡

የአማራ ክልል ኮሚኒኬሽን ጉዳዩች ጽ/ቤት በበኩሉ በፌደራል መንግስት ድጋፎች የተደረጉ ቢሆንም  ተፈናቃዮቹ ላይ ከደረሰው ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ እና ስነ ልቦናዊ ችግር አንፃር በቂ አለመሆኑን  ተናግረዋል፡፡

የክልሉ ኮሚኒኬሽን ጉዳዩች ዳይሬክተር አቶ አሰማኸኝ አስረስ ከፌደራል መንግስት የተደረገው ድጋፍ ከተፈናቃዮች ቁጥር እና የጉዳት መጠን አንፀር ሲታይ ድጋፉ በቂ አይደለም ብለዋል፡፡

ለተፈናቃዮቹም ድጋፍ ማሰባሰቢያ የባንክ ሂሳብ መከፈቱ እና በቅርቡም በአጭር የፅሁፍ መልዕክት ገቢ ማሰባሰቢያ መስመር ይፋ ይደረጋል ነው ያሉት።

Write a Reply or Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *