loading
ኢትዮጵያ ባለፉት ስምንት ወራት ውስጥ ወደውጭ በላከችው ቡና 433 ሚሊዮን የሚጠጋ የአሜሪካ ዶላር አገኘች

ኢትዮጵያ ባለፉት ስምንት ወራት ውስጥ ወደውጭ በላከችው ቡና 433 ሚሊዮን የሚጠጋ የአሜሪካ ዶላር ማግኘቷ ተገለጸ።

የተላከው ቡና እና የተገኘው ገቢ አስቀድሞ ከተያዘው እቅድ ጋር ሲነጻጸር ቅናሽ አሳይቷል ተብሏል።

የኢትዮጲያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን  ለአርትስ በላከው የ 2011 በጀት አመት   ያለፉት ስምንት ወራት የቡና ፤ሻይ እና  ቅመማ ቅመም  ኤክስፖርት አፈፃፀም ሪፖርት እንደሚያመለክተው   በበጀት ዓመቱ ስምንት ወራት 168 ሺህ 336 ቶን የቡና ምርት በመላክ 607.7 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር ገቢ ለማግኘት ታቅዶ የነበረ ቢሆንም 130 ሺህ 472 ቶን ቡና በመላክ  423 ሚሊየን የአሜርካን ዶላር የሚጠጋ ገቢ ተገኝቷል፡፡  እንደሪፖርቱ ገለጻ የተላከው ቡና መጠን ከዕቅዱ ጋር ሲነጻጸር ወደ23 በመቶ ቅናሽ አሳይቷል።

ባለስልጣኑ በአጠቃላይ የላከው የቡና ምርት መጠን አንጻር ሲታይ አፈፃፀሙ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር ወደ 7 ሺህ ቶን አካባቢ ቅናሽ ያሳየ ሲሆን  በገቢ ደረጃም የ 59 ሚልዮን ዶላር አካባቢ  ቅናሽ አስመዝግቧል።

በምርት በኩል ሲታይ ባለፈው ነሃሴ ወር ከፍተኛ የቡና ምርት የተገኘበት ሲሆን ህዳር ደግሞ ዝቅተኛ ገቢ የተገኘበት ወር እንደነበር ሪፖርቱ ያስረዳል።በገቢ ረገድም በተመሳሳይ ነሃሴ ከፍተኛ ህዳር ደግሞ ዝቅተኛ ገቢ የተገኘባቸው ወራቶች መሆናቸው ተመልክቷል።

ባሳለፍነው የካቲት ወር 20,343.59 ቶን የቡና ምርት ወደውጭ ሃገር ገበያ በመላክ 73 ነጥብ 38 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር ገቢ ለማግኘት ታቅዶ ከዕቅዱ 79 ነጥብ 63 በመቶ በመላክ 55 ነጥብ 31 ሚሊየን የአሜርካን ዶላር መገኘቱም ሪፖርቱ ላይ ተመልክቷል።

እንደሪፖርቱ በአጠቃላይ ስምንት ወራት ውስጥም ይሁን በየካቲት ወር የቡና ምርትን ወደውጭ ሃገር በመላክ በኩል አፈፃፀሙ ከእቅዱ ጋር ሲናበብ ዝቅተኛ ሆኖ ተገኝቷል። በገቢ በኩልም ሃገሪቱ ከዚህ ምርት እያገኘች ያለችው የገንዘብ መጠን ከታቀደው በታች መሆኑን ነው ሪፖርቱ የሚያመላክተው።

Write a Reply or Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *