loading
በአውሮፕላኖቹ ላይ ምንም አይነት የቴክኒክ ችግር እንደሌለ ሲሟገት የነበረው ቦይንግ ኩባንያ 737-8 ማክስ አውሮፕላኖቹን በሙሉ ማገዱ እያነጋገረ ነው

በአውሮፕላኖቹ ላይ ምንም አይነት የቴክኒክ ችግር እንደሌለ ሲሟገት የነበረው ቦይንግ ኩባንያ 737-8 ማክስ አውሮፕላኖቹን በሙሉ ማገዱ እያነጋገረ ነው

በርካታ ቁጥር ያላቸው ሀገራት ቦይንግ 737-8 ማክስን ሲያግዱ የአሜሪካ ፌዴራል አቪየሽን አስተዳደር ግን አውሮፕላኖቹ አስተማማኝ ናቸው ለበረራም ብዙ ናቸው በማለት በእምቢተኝነት መጽናቱም ይታወሳል።

ታዲያ የቦይንግ ኩባኒያ እና የአሜሪካ ፌዴራል አቪየሽን አስተዳደር ሃሳባቸውን ምን አስቀየራቸው?

ግዙፉ የአውሮፕላን አምራች ቦይንግ ኩባኒያ ቦይንግ 737-8 ማክስ 8 እና 9 የተባሉትን እና ገበያውን በቅርቡ የተቀላቀሉትን  አውሮፕላኖቹን በሙሉ ከበረራ አግዷል፡፡

ኩባንያው እንዳሳወቀው ያሉትን 371 ማክስ 8 አዳዲስ አውሮፕላኖች በሙሉ ነው ከበረራ ያገደው ፡፡

በርካታ ቁጥር ያላቸው ሀገራት ቦይንግ 737-8 ማክስን ሲያግዱ አስተዳደሩ ግን እገዳውን አልቀበልም ማለቱ ይታወሳል፡፡

በተመሳሳይ የአሜሪካ ባለስልጣናት እና ሴናተሮች ለሀገሪቱ ሲቪል አቬሽን ባለስልጣን የቦይንግ ስሪት የሆኑት እነዚሁ አውሮፕላኖች ከበረራ እንዲታገዱ ሀሳብ ቢያቀርቡም ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ አውሮፕላኖቹን ለማገድ ፍላጎት አላሳየም ነበር፡፡

እንደውምየባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ኃላፊ ዳንኤል ዊል  “ስለ አውሮፕላኖቹ ደህንነት የሚያሰጋ ማስረጃ ከየትኛውም አየርመንገድ አልደረሰንም፡፡ አሁን ላይ አውሮፕላኖቹ ከበረራ እስከ መታገድ የሚያደርስ ስጋት የለባቸውም” በማለት ባለስልጣኑ እገዳውን እንደማይቀበል ማስታወቃቸው ይታወሳል፡፡

አሁን ግን የአሜሪካ ፌዴራል አቪየሽን አስተዳደር “አደጋው በደረሰበት ቦታ ላይ የተገኙ አዳዲስ መረጃዎች እና የተጣሩ የሳተላይት ምስሎች  በጊዜያዊነትም ቢሆን  የእግድ ውሳኔውን እንዳስተላልፍ ምክንያት ሆኖኛል”  ሲል ሃሳቡን መቀየሩን አስታውቋል።

በግልፅ ለዚህ ምክንያት ሆኖኛል ያላቸው የሳተላይት መረጃዎች ግን አስተዳደሩም ይሁን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ይፋ አላደረጉም፡፡

 

እንደ ዳንኤል ዊል ገለፃ የተከሰከሰው የኢትዮጵያ አየር መንገድ  አውሮፕላን ከዚህ ቀደም መሰል አደጋ ከደረሰበት የኢንዶኔዢያ ላየን አየር መንገድ አውሮፕላን አደጋ ጋር ተመሳሳይ ነው ።በተጨማሪም የመከስከስ አደጋው በደረሰበት ቦታ ላይ የተገኙት መረጃዎች በላየን አየር መንገድ ከደረሰው ዕጣ ፈንታ ጋር ተመሳሳይ መሆኑን የሚያሳይ ነው” ማለታቸው ቦይንግ ለአደጋዎቹ መንስኤ የሆነው አዲሶቹ ምርቶቹ ላይ የተፈጠረው የቴክኒክ ችግር እንደሆነ ያመነ ይመስላል የሚል አስተያየት እየተሰነዘረበት ነው፡፡

ቦይንግ ኩባንያ የ157 ሰዎችን ህይወት ከቀጠፈው አሳዛኝ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አደጋ በኃላ ገበያው በእጅጉ ተቀዛቅዟል፡፡  ኩባንያው ከአደጋው በኃላ እስካሁን ባሉት ቀናት 26.65 ቢሊየን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ እንዳጣ ሮይተርስ ዘግቧል፡፡

በትላንትናው እለት ደግሞ  የካናዳ ትራንስፖርት ሚኒስትር ስለ አደጋው አዲስ መረጃ አግኝቻለሁ ማለቱን ተከትሎ ቦይንግ 737-8 ማክስ አውሮፕላኖቸን ከበረራ አግዳለች።

እንደ መረጃውም በቅርቡ የተከሰከሰው ቦይንግ 737 ማክስ 8ና ካናዳ ውስጥ አገልግሎት እየሰጡ ያሉት 737 ማክስ አውሮፕላኖች ተመሳሳይ የበረራ ችግር ማሳየታቸውን ይፋ አድርገዋል።

ከዚሁ ጋር ተያይዞ ታይም መፅሄት በድረገፁ ይዞት የወጣው ዘገባ ባሳለፍነው የፈረንጆቹ አመት አሜሪካውያን ፓይለቶች ቢያንስ በሁለት በረራዎች ላይ እንግዳ የሆነና ለአደጋ አጋላጭ ክስተት አጋጥሟቸው ጉዳዩን ሪፖርት አድርገው እንደነበር ይገልፃል፡፡

የፓይለቶቹ ሪፖርት እንደሚለው አውሮፕላኑ በራሱ የሚበርበት የአውቶ ፓይለት ስርዓት ድንገት አውሮፕላኑ አፍንጫውን ወደ መሬት እንዲያዘቀዝቅ ሲያደርግ በፍጥነት ደርሰው የአውሮፕላኑን አውቶፓይለት አላቅቀው  ወደ ላይ እንዲወጣ እንዳደረጉ ይገልፃል፡፡

የታይም ዘገባ እንደሚለው፣ በአውሮፕላኑ ላይ ለአደጋ የሚያጋልጥ ችግር አየን ያሉት ፓይለቶች ሪፖርትን የሰበሰበው የአሜሪካው የሕዋ ምርምር ተቋም ናሳ ሲሆን የፓይለቶቹ ሥም፣ የአየር መንገዶቹ ማንነት እና ሁኔታው ያጋጠመበት የአየር ክልል አልተጠቀሰም ተብሏል፡፡

ፓይለቱ ሁኔታውን አስመልክቶ እንደተናገረው አውሮፕላኑ መነሳት እንደጀመረ ወዲያው  በደቂቃ ከ365 እስከ 460 ሜትር በሆነ ፍጥነት ወደ ምድር ሲወርድ ማየቱን ፣የፓይለቶቹ ክፍል ውስጥ ያለው ማስጠንቀቂያም እንደተሰማ ፣ይህንንም ተከትሎ ፓይለቱ አውቶፓይለቱን አጥፍቶ አውሮፕላኑን ወዲያው ወደላይ ከፍ እንዲል እንዳደረገ ሰፍሯል፡፡

አውሮፕላኑ ድንገት አፍንጫውን ወደታች የሚያደርግበት ምንም ምክንያት ሊኖር አይችልም  ማለቱም ተጠቅሷል፡፡

ምንም እንኳ ቦይንግ ጣቱን ወደ አብራሪዎቹ ቢቀስርም  ከነዚህ ሁሉ ክስተቶች ጀርባ አለ የሚባለው  በማክስ 8 አውሮፕላኖች ላይ የተገጠመው አዲስ የአውሮፕላኑ “አንቲ ስቶል” የሚባል የኮምፒውተር ስርዓት ነው፡፡

ሆኖም ግን የሁለቱም አውሮፕላኖች አደጋ እና በአውሮፕላን አብራሪዎቹ የተገለጹት ችግሮች  በዝርዝር እስኪጣራ ድረስ ከመላ ምት በዘለለ የአደጋው መንስዔ ይህ ነው ብሎ መናገር እንደማይቻል ባለሞያዎች ይናገራሉ፡፡


በተያያዘ መረጃም የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከተከሰከሰው ቦይንግ 737 አውሮፕላን የተገኘውን ጥቁር የመረጃ መዝጋቢ ሳጥን  ብላክ ቦክስ  ለማስመርመር ወደ ፈረንሳይ ልኬዋለሁ ብሏል።

መጀመሪያ የመረጃ ሳጥኑን እንድትመረምር ጥያቄ የቀረበላት ጀርመን  ነበረች፡፡ ነገር ግን የመመርመሪያ ሶፍትዌሩ  እንደሌላት በመግለፅ ጥያቄውን ሳትቀበል መቅረቷ ተገልፃል።

የመረጃ ሳጥኑ ወደ ፓሪስ የሄደው በአለም አቀፉ አቪዬሽን አደጋ ምርመራ ቢሮ በሚመራው የኢትዮጵያ ልዑክ ነው። የምርመራ ውጤቱ ከውስብስብ የአቪየሽን ፖለቲካ ነጻ ሆኖ የበርካቶችን ህይወት የቀጠፈው አደጋ ምክንያት እስከሚታወቅ በዚህ ዙሪያ የሚወጡ መረጃዎችን አርትስ ቲቪ ተከታትሎ ወደእናንተ ያደርሳል፡፡

Write a Reply or Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *