loading
“በዛሬው እለት ቦሌ አካባቢ ተከስቶ የነበረው የጸጥታ ችግር የቡድን ጸብ እንጂ የፖለቲካ ግጭት አይደለም ” የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን

“በዛሬው እለት ቦሌ አካባቢ ተከስቶ የነበረው የጸጥታ ችግር የቡድን ጸብ እንጂ የፖለቲካ ግጭት አይደለም ” የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን።

በዛሬው ዕለት አዲስ አበባ ውስጥ በተለምዶ ቦሌ ሚካኤል ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ተፈጥሮ የነበረው የጸጥታ ችግር ተራ የቡድን ጸብ እንጂ ከፖለቲካ ግጭት ጋር የተገናኘ እንዳልሆነ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።

በቡድን ጸቡ ተካፋይ የነበሩትን 231 ተጠርጣሪዎች በሙሉ በቁጥጥር ስር አውሎ ባደረገው ማጣራት ከጉዳዩ ጋር ቀጥታ ግንኙነት አላቸው የተባሉ 72 ወጣቶችን በማስቀረት ቀሪዎቹን 159 ወጣቶች በምክር መልቀቁንም አስታውቋል።

የፖሊስ ኮሚሽኑ የኢንዶክትሪኔሽን እና የህዝብ ግንኙነት ምክትል ዳይሬክተር ኮማንደር ፋሲካ ፈንታ ማምሻውን ለአርትስ ቲቪ እንዳስታወቁት በወጣቶቹ መካከል የተፈጠረውን ጸብ ከቄሮ የወጣቶች ቡድን ጋር በማገናኘት የፖለቲካ ግጭት አስመስሎ የተናፈሰው ወሬ ፍጹም መሰረተ ቢስ ነው።

እንደኮማንደር ፋሲካ ገለጻ የጸቡ መነሻ በአንድ የላዳ ታክሲ ሹፌር እና  በአካባቢው በነበሩ ወጣቶች መካከል “መንገድ አሳልፈኝ አላሳልፍም” በሚል ጭቅጭቅ የተነሳ አለመግባባት ነው።

ትናንት መጋቢት 8 ቀን 2011 ዓ.ም ከቀኑ 10 ሰዓት አካባቢ በቦሌ ክፍለከተማ ወረዳ አንድ ክልል አየርአምባ ትምህርት ቤት ከፍ ብሎ በሚገኘው የጫት መሸጫ ሱቆች አካባቢ ተከስቶ በነበረው በዚሁ ተራ ግጭት ቂም የያዘው የታክሲ ሹፌር ወደሰፈሩ በመሄድ ለጓደኞቹ በአካባቢው ወጣቶች ጥቃት እንደደረሰበት ተናግሮ ለጸብ ሲዘጋጁ ካደሩ በኋላ በዛሬው ዕለት ወደስፍራው በመምጣት አጥቅተውኛል ካላቸው ወጣቶች ጋር ግጭት እንዲፈጠር አድርጓል።

እንደኮማንደር ፋሲካ ገለጻ ፖሊስ አስቀድሞ መረጃ ስለደረሰው ወደስፍራው ሃይል በማሰማራት ጸቡን ለመከላከል ጥረት በማድረግ ላይ እያለ በሁለቱ ሰፈር ወጣቶች መካከል በተቀሰቀ ጸብ በእንቅስቃሴ ላይ የነበሩ ሶስት ተሽከርካሪዎች መስተዋት ሲሰበር በተመሳሳይ  በመስተዋት ተሰርተው የነበሩ የጫት መሸጫ ሱቆች እና በአካባቢው በሚገኝ የኦሮሚያ ባንክ ቅርንጫፍ ቢሮ መስተዋት ላይም መጠነኛ ጉዳት ደርሷል።

ፖሊስ በሁለቱም ወገን የጸቡ ተካፋይ ናቸው ያላቸውን 231 በቁጥጥር ስር አውሎ ምርመራ ማጣራቱንና በቀጥታ በግጭቱ ተሳታፊ ናቸው ያላቸውን 67 ወንዶችና 5 ሴቶች በድምሩ 72 ተጠርጣሪዎች በእስር አቆይቶ ቀሪዎቹን 159 ተጠርጣሪዎች በሙሉ ዳግም በዚህ አይነት ጥፋት ላይ እንዳይገኙ መክሮ መልቀቁን ተናግረዋል።

ኮማንደር ፋሲካ እንዳሉት እውነታው ይኸው ሆኖ ሳለ አንዳንድ አክቲቪስቶች በማህበራዊ ሚዲያ “በቦሌ ቄሮ እና በአዲስ አበባ ወጣቶች መካከል ግጭት ተቀሰቀሰ” በማለት ባሰራጩት የሃሰት መረጃ ያልተገባና ለፖለቲካ አላማ የታቀደ ተግባር በመፈጸም  የህብረተሰቡን ደህንነት ስጋት ውስጥ ለመክተት ሞክረዋል። ከተማዋ አለመረጋጋት እንደሌላት በማሰብ ብዙዎች ለደህንነታቸው ስጋት እንዲገባቸውም ምከንያት ሆነዋል። ይህ ተግባር ፍጹም ሃላፊነት የጎደለውና ማመዛዘን ከሚችል አካል የማይጠበቅ ነው ያሉት ኮማንደሩ እንዲህ አይነት የሃሰት መረጃ የሚያሰራጩ ግለሰቦችም በህዝብ ሰላምና ደህንነት ላይ ከፍተኛ ወንጀል እየፈጸሙ መሆኑን ሊገነዘቡና ሊጠነቀቁ ይገባል ነው ያሉት።

ህብረተሰቡም በዚህ አይነት የፈጠራ መረጃ እንዳይደናገር ያሳሰቡት የፖሊስ ሃላፊው ለማይበርድ ግጭት የሚዳርጉ የሃሰት ወሬዎችን ባለማራገብ ሰላሙን እንዲጠብቅ መልዕክት አስተላልፈዋል። የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ከዚህ ግጭት ምርመራ ጋር ተያይዞ ያሉትን ቀሪ ውጤቶች በቀጣይ ለህዝቡ ይፋ እንደሚያደርግም  ኮማንደር ፋሲካ  ተናግረዋል።

Write a Reply or Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *