Uncategorized

የመንግስት የልማት ድርጅቶችን ወደ ግል የማዛወሩ እቅድ የሚፈለገውን ውጤት አላስገኘም ሲሉ አንዳንድ ሰራተኞች ቅሬታ አቀረቡ

የመንግስት ልማት ድርጅቶች ወደግል ሲዘዋወሩ መንግስት ለሰራተኞቹ እና ለድርጅቱ ተገቢውን ክትትል እንደማያደርግ ወደ ግል የተዘዋወሩት እና ለኪሳራ የተዳረጉት ድርጅቶች ለአርትስ ገልፀዋል፡፡

በተቃራኒው መንግስት የመንግስት የልማት ድርጅቶችን ወደግል ባለሃብቶች  ሳዘዋውር በጥንቃቄ እና በክትትል  ነው ይላል፡፡

በመንግስት ስር የሚገኙ  እንደ ባቡር ፣ የስኳር ልማት፣ የኢንዱስትሪ ፓርክ፣ የሆቴልና የተለያዩ የማምረቻ ድርጅቶች ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል በአክሲዮን ሽያጭ ወደ ግሉ ዘርፍ እንዲተላለፉ መወሰኑ ከተሰማ ዘለግ ያለ ጊዜ ተቆጥሯል።

ከጥቅምት 2011 አ.ም ጀምሮም መንግስት የፕራይቬታይዜሽን ፖሊሲውን  ከከለሰ ወዲህም ኢትዮ ቴሌኮም፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫዎችና የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ድርጅት ትልቁን የአክስዮን ድርሻ መንግስት ይዞ፤ ቀሪው አክሲዮን ለሀገር ውስጥና ለውጭ ባለሃብቶች እንዲተላለፍ  ውሳኔ ላይ መደረሱም የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው።

መንግስት ይህንን ሲያደርግ የልማት ድርጅቶቹን  ወደ ግል በማዞር  ወይም ፕራይቬታይዝ በማድረግ ላይ  ከ 15 አመት በላይ ልምድ አለኝ ይላል፡፡ በ10 አመት ዉስጥም 370 ድርጅቶችን ወደ ግል ዘርፍ እንዳዘዋወረ ከመንግስት ልማት ድርጅቶች ኤጀንሲ ያገኘነው መረጃ ያሳያል፡፡

ምንም እንኳ መንግስት የአገሪቱ ዋነኛ የዉጭ ምንዛሬ ማስገኛ መንገዶች የሆኑት ግብርና እና የማምረቻ  ኢንዱስትሪዉ ዘርፍ ያስገኛሉ የተባለዉ የዉጭ ምንዛሬ መጠን አነስተኛ አፈፃፀም በማሳየቱ  የልማት ድርጅቶችን ወደ ግል ማዘዋወር የተሻለ ምርታማ እና ትርፋማ ለመሆን ያስችላል የሚል መንገድ የዞ እሱኑ እየተገበረ ይገኛል።

ያም ሆኖ ወደ ግል ባለሃብቶች ከተዘዋወሩ ድርጅቶች ውስጥ ስኬታማ  እና ትርፋማ የሆኑ እንዳሉ ሁሉ ለከፍተኛ ኪሳራ ተዳርገው ሰራተኞቻቸውን የበተኑና ድርጅቶቹን የዘጉም መኖራቸው ሃቅ ነው።

ይህንን መሰረት አድርገው ለአርትስ ቲቪ ቅሬታቸውን ያቀረቡ፣ ምስላቸውና የሚሰሩበት ተቋም ይፋ እንዳይደረግባቸው የጠየቁ ሰራተኞችና ሃላፊዎች መንግስት የልማት ድርጅቶችን ወደግል ሲያዞር ቀጣይ ትርፋማነታቸውን እና የሰራተኞቹን መብት አጠባበቅ አስቀድሞ በማቀድ  ስለማይከታተል የድርጅቶቹ ምርታማነትና ከመቀነስ አልፎ ለኪሳራ እንዲዳረጉ ምክንያት ሆኗል በማለት ይወቅሳሉ። ይህ ክስተት መንግስት ድርጅቶቹን ወደግል ለማዞር ምክንያት ሆኖኛል ከሚለው ምርታማነትን የመጨመር እቅድ ጋር ሲተያይ ተቃራኒ ውጤት እያመጣ ነው በማለትም ይተቻሉ።

በፕራይቬታይዜሽን ትግበራው የልማት ድርጅቶችን ከመንግስት ከተረከቡ ከጥቂት አመታት በኋላ የከሰሩ ድርጅቶች መኖራቸው ሃቅ ነው። እንደአብነት በማምረቻው ዘረፍ ታዋቂ  እና ምርቶቹም  በጣም ተፈላጊ የነበረው አቃቂ ቆርቆሮ ፋብሪካን ማንሳት ይቻላል፡፡

አቃቂ ቆርቆሮ ፋብሪካ በ2002 አ.ም ባዘቶ ኢንደስትሪያል ለተሰኘ የግል ድርጅት ነበር የተሸጠው፡፡

ፋብሪካው በመንግስት ይዞታ ስር በነበረበት ወቅት ትርፋማ እንደነበር ሰራተኞቹ እና የቀድሞ አመራሮቹ ለአርትስ ተናግረዋል።

በቴሌቭዥን ስክሪን ላይ መታየት ያልፈለጉት የባዘቶ ኢንደስትሪያል ማኔጂንግ ዳይሬክተርም አቃቂ ቆርቆሮ ፋብሪካ መክሰሩን ለአርትስ አረጋግጠዋል። ለዚህም ከውጭ የሚመጣው ጥሬ እቃ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ በመጠየቁ እና ድርጅቱም የገንዘብ እጥረት ስላጋጠመው   ነው ብለዋል፡፡

የድርጅቱ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ፋብሪካው በመንግስት ይዞታስር በነበረበት ወቅት ያገኝ የነበረው የጥሬ እቃ ፣የውጭ ምንዛሬ እና ሌሎችም ጥቅማጥቅሞች አሁን በኛ እጅ ስር በገባበት ወቅት ስለቀረ ነው ለኪሳራ የተዳረግነው ባይ ናቸው።  ይህንን ሃሳብ የሚቃወሙት የመንግስት ልማት ድርጅቶች ኤጀንሲ የኮርፖሬት ኮሚኒኬሽን ዳይሬክተሩ ግን የትኛውም በመንግስት ይዞታስር ያለ ድርጅት የተለየ የሚያገኘው ድጋፍም ሆነ ጥቅም የለም ይላሉ፡፡

አቃቂ ቆርቆሮ ፋብሪካን ለዋቢነት አነሳን እንጂ በመንግስት ይዞታ ስር በነበሩበት ወቅት ትርፋማ የነበሩ ወደ ግል ዚዛወሩ ግን ለኪሳራ የተዳረጉ ሌሎችም ድርጅቶች አሉ፡፡ይህ ማለት ግን ስኬታማ እና ትርፋማ የሆኑ ተቋማት የሉም ማለት አይደለም።  ነገር ግን የመንግስት የልማት ድርጅቶችን ወደ ግል ባለሀብቶች ሲዘዋወሩ ሊታዩ የሚገባቸውና ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚያሻቸው ጉዳዮች እንዳሉ ነው አስተያየቶች የሚሰጡት።

ሌላው ከዚህ ወደ የመንግስት ልማት ደርጅትን ወደግል ይዞታ ከማዘዋወር ጋር በስፋት የሚነሳው ነገር አንድ ቡድን የልማት ድርጅቶችን እየገዛ እንዲጠቀም ይደረጋል የሚለው ቅሬታ ነው። ከዚህ ቀደም እንደነ ኢፈርት ያሉ የገዢው ፓርቲ እህት ድርጅቶች ንብረት የሆኑ ተቋማት በዚህ የመንግስት ድርጅቶችን የመጠቅለል ተግባር ሲታሙ እንደነበረ ሁሉ አሁንም የአሰላ ብቅል ፋብሪካ የተሸጠው ለገዢው ፓርቲ ቡድን ነው የሚሉ ትችቶች አሉ፡፡

በኤጀንሲው በኩል የተሰጠው ምላሽ ግን ይህ ወሬ ከእውነት የራቀ ነው የሚል ነው። መንግስት እስከአሁን ወደ ግል ባለሃብቶች በተዘዋወሩ ድርጅቶች 49.1 ቢሊዮን ብር ገቢ ማግኘቱን ሰምተናል፡፡ ሸበሌ ትራንስፖርት፣ የኢትዮጵያ ፐልፕ እና ወረቀት ፋብሪካ፣ ብሄራዊ አልኮል እና አረቄ ፋብሪካ ለግል ባለሃብቶች ለመሸጥ በሂደት ላይ ካሉ ድርጅቶች ውስጥ ተጠቃሾች ናቸው፡፡

በቅርቡ 75 በመቶ ድርሻው ወደ ግል ባለሀብቶች የተዘዋወረው የኮርኪ እና ጣሳ አክሲዮን ማህበር እና የአሰላ ብቅል ፋብሪካ በቅርቡ ሂደታቸው ተጠናቆ ወደ ግል ባለሃብቶች ከተዛወሩ ድርጅቶች መካከል ተጠቃሾች ናቸው ፡፡

 

Related Articles

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Back to top button