loading
በቦሌው የቡድን ጸብ ተካፋይ ነበሩ የተባሉ ተጠርጣሪዎች በሙሉ ተገቢው ምክር ተሰጥቷቸው መለቀቃቸውን ፖሊስ አስታወቀ

በተለምዶ ቦሌ ሚካኤል ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ተከስቶ በነበረው የቡድን ጸብ ላይ ተሳትፈዋል በማለት በቁጥጥር ስር ያዋላቸውን ተጠርጣሪዎች ሙሉ በሙሉ መልቀቁን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሸን አስታወቀ።

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የኢንዶክትሪኔሽን እና የህዝብ ግንኙነት ምክትል ዳይሬክተር ኮማንደር ፋሲካ ፈንታ ለአርትስ ቲቪ እንደተናገሩት ተፈጥሮ የነበረው የጸጥታ ችግር ተራ የቡድን ጸብ እንጂ ብዙዎች በማህበራዊ ሚዲያ እንዳራገቡት ከፖለቲካ ግጭት ጋር የተገናኘ አይደለም።

በስፍራው የደረሰው ፖሊስ በቡድን ጸቡ ተካፋይ የነበሩትን 231 ተጠርጣሪዎች በሙሉ በቁጥጥር ስር አውሎ ባደረገው ማጣራት ከጉዳዩ ጋር ቀጥታ ግንኙነት አላቸው የተባሉ 72 ወጣቶችን በማስቀረት ቀሪዎቹን 159 ወጣቶች በምክር እንደለቀቃቸው  መግለጹን አስታውሰዋል።

በአንድ የላዳ ታክሲ ሹፌር እና  በአካባቢው በነበሩ ወጣቶች መካከል “የንግድ በር ዘጋህብኝ ” በሚል ጭቅጭቅ በተነሳ አለመግባባት ተከስቷል የተባለው ይኸው ተራ ግጭት በንብረት ላይ መጠነኛ ጉዳት ከማስከተሉ በቀር በሰው አካልም ይሁን ህይወት ላይ ያደረሰው ጉዳት እንደሌለም ጨምረው ገልጸዋል።

በወጣቶቹ መካከል የተፈጠረውን ጸብ ከቄሮ የወጣቶች ቡድን ጋር በማገናኘት የፖለቲካ ግጭት ለማስመሰል የተሞከረው ሙከራ ሃላፊነት የጎደለውና ጸብ አባባሽ ተግባር ነው ያሉት ኮማንደሩ ፖሊስ ይህንኑ መሰረት በማድረግ በማረፊያ ቤት አቆይቷቸው የነበሩትን ወጣቶች ማነጋገሩንም ኮማንደሩ ጠቅሰዋል።

በመሆኑም ፖሊስ በማረፊያ ቤት አቆይቷቸው የነበሩትን 72 ወጣቶች በሙሉ ተገቢውን ምክር በመስጠት በነጻ ለቅቋቸዋል ነው ያሉት ኮማንደር ፋሲካ ።

ህብረተሰቡ በማህበራዊ ሚዲያ የሚናፈሰውን እና ለግጭት በር የሚከፍተውን የሃሰት ዜና ባለማራገብ የሰላም መደፍረስ እንዳይከሰት የበኩሉን ድጋፍ ሊያደርግ ይገባልም ብለዋል።

 

Write a Reply or Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *