loading
የአደጋው ምክንያት የአውሮፕላኑ የቴክኒክ ችግር ሆኖ ከተገኘ ቦይንግ ለሟቾች ከባድ የካሳ ክፍያ መፈጸም ይጠብቀዋል እየተባለ ነው

በሰሞኑ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራ ቁጥር ኢቲ 302 የተመዘገበውና ቢሾፍቱ አካባቢ የመውደቅ አደጋ የደረሰበት ቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላን ምርመራ ሲጠናቀቅ የአደጋው ምክንያት የአውሮፕላኑ የቴክልኒክ ችግር ሆኖ ከተገኘ ቦይንግ ኩባንያ ለደረሰው የሰው ህይወት ህልፈት ከባድ ካሳ ከፍያ ይጠብቀዋል እየተባለ ነው።

እስከአሁን የወጡት መረጃዎች ከአሜሪካው አዲሱ  የቦይንግ አውሮፕላን ምርት የቴክኒክ ችግር ጋር የተያያዘ  እንደሆነና  ከ6 ወራት በፊት ባህር ላይ ከተከሰከሰው የኢንዶኔዥያው ቦይንግ አውሮፕላን  አደጋ ጋር እንደሚመሳሰል የሚጠቁሙ ናቸው፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት ትራንስፖርት ሚኒስቴር ሰሞኑን እንዳረጋገጠው የመረጃ ሳጥኑ ( ብላክ ቦክሱ) ም ይህንኑ የሚያረጋግጥ መረጃ ሰጥቷል።

ሮይተርስ እንደዘገበው ይህ ምርመራ ሲጠናቀቅ የአደጋው መንስዔ ቦይንግ ያመረተው እና አደጋ የደረሰበት አውሮፕላን ስሪት ወይም ማሻሻያ ሆኖ ከተገኘ  ቦይንግ ኩባንያ ከባድ ካሳ ይጠብቀዋል።

እንደ ህጉ እና እንደ ምርመራው ሊቀንስ አልያም ሊጨምር ቢችልም የቦይንግ ኩባንያ ለአንድ በአደጋው ምክንያት ህይወቱ ላለፈ ሰው ከሁለት እስከ 3 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ካሳ ለሟች ቤተሰቦች መክፈሌ አይቀሬ ይሆናል።

በዚህም መሰረት በኢትዮጵያ አየር መንገድ ቢሾፍቱ አካባቢ በቦይንግ 737 ኤት ማክስ አውሮፕላን በመከስከስ አደጋ ህይወታቸውን ላጡ 157 ሰዎች ቤተሰብ ከ25 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ ካሳ ሊከፍል ይገደዳል ይላል የሬውተርስ ዘገባ ፡፡

8 አሜሪካዊያን በዚሁ  በቢሾፍቱ በቦይንግ 737 ኤት ማክስ አውሮፕላን መከስከስ አደጋ እንደሞቱ ይታወሳል፡፡

ኒውዮርክ ታይምስ በበኩሉ የህግ ባለሞያዎችን ጠቅሶ እንዳለው የአሜሪካዊያኑ ሟቾች የካሳ ጉዳይ በአሜሪካ ፍርድ ቤት የሚታይ በመሆኑ ኢትዮጵያዊያኑን ጨምሮ የሞት አደጋ ለደረሰባቸው ሌሎች ሀገራት  ዜጎች ቦይንግ ሂደት በአሜሪካ ፍርድቤት በሚታይ ችሎት ካሳውን እንዲከፍል ሳይገደድ አይቀርም።

የሟች ወገኖች የካሳ የመነሻ ክፍያ በኢትዮጵያ አየር መንገድ የሚፈጸም ቢሆንም የአውሮፕላን መከስከስ አደጋው ያጋጠመበት ምክንያት በቦይንግ አውሮፕላን ስሪት የቴክኒክ  ችግር መሆኑ ከተረጋገጠ  ግን በህጉ መሰረት ቦይንግ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የከፈለውን የመጀመሪያ የካሳ ክፍያ ጭምር እንዲያወራርድ ይጠበቅበታል።

በዚህ አደጋ ሳቢያ በርካታ አለም አቀፍ አየር መንገዶች ቦይንግ አዲሶቹን ምርቶች እንዲያቀርብላቸው ያዘዙትን ትእዛዝ ሰርዘዋል። አምራቿ አሜሪካን ጨምሮ የ41 ሀገራት አየር መንገዶች ምርቶቹን ከበረራ አግደዋል፡፡ በዚህ ሳቢያ ለደረሰባቸው ኢኮኖሚያዊ ጉዳት ቦይንግ ኩባንያን ካሳ የጠየቁ አየር መንገዶችም አልጠፉም፡፡ ለምሳሌ የኖርዌይ አየር መንገድ የቦይንግ 737 ማክስ ኤት አውሮፕላኖች ላይ እንዳይበሩ እገዳ ከጣለ በኋላ  ለሚገጥመው ኪሳራ ከቦይንግ ኩባኒያ ካሳ እንደሚፈልግ ገልፆ ነበር፡፡

የአየር መንገዱ ስራ አሰፈፃሚ ቦጆርን ጆስ ጉዳዩ እስኪጣራ ድረስ ላቆምናቸው አውሮፕላኖች እኛ ተጠያቂ ልንሆን በሱ ሳቢያም ኪሳራ ልንገባ አይገባም ፤ አውሮፕላኑ ከበረራ ውጭ በመሆኑ ሳቢያ እየደረሰ ያለውን እያንዳንዷን ኪሳራ ያመረተው ኩባንያ ሊያካክስልን ግድ ይለዋል ሲሉ ለሲኤንኤን ገልፀው ነበር።

የቦይንግ ምርት የሆነው ቦይንግ 737 ማክስ ኤይት አውሮፕላን በቢሾፍቱ መከስከሱን ተከትሎ ቦይንግ ኪሳራ እየገጠመው ነው።  ባሳለፍነው ሳምንት እንኳ ዓለም አቀፍ አክሲዎን ድርሻው በ13 በመቶ ቀንሷል፡፡

የመረጃ ሳጥኑ የምርመራ ውጤት  ሲጠናቀቅ በተባበሩት መንግስታት የአለም አቀፉ የአቬዬሽን ጉዳይ መምሪያ የቦይንግ ኩባንያን ህልውና  ይወስናል የተባለለትን ውሳኔ ያሰማል።

Write a Reply or Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *