Uncategorized

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ለይፋዊ የስራ ጉብኝት ኳታር ገብተዋል

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ለይፋዊ የስራ ጉብኝት ኳታር ገብተዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተመራው የልዑካን ቡድን ዶሃ ሲደርስ የኳታር የትራንስፖርት እና መገናኛ ሚኒስትር ጃሲም ቢን ሳይፍ አል ሱለይቲ አቀባበል አድርገውለታል።

በጉብኝታቸውም ከሃገሪቱ ኤሚር ሼክ ታሚም ቢን ሃማድ አል ታኒ ጋር በሁለትዮሽና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ይወያያሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ከዚህ ባለፈም በሁለትዮሽ ትብብር እና  የልማት ጉዳዮች ላይ ይመክራሉ ተብሎም ይጠበቃል።

የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት እየተሻሻለ ሲሆን፥ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉብኝትም የሃገራቱን ግንኙነት ወደተሻለ የትብብር ምዕራፍ እንደሚያሸጋግረው ታምኖበታል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ወደ ስልጣን ከመጡ ወዲህ የመጀመሪያቸው የሆነው የኳታር ጉብኝት፥ ለሃገራቱ ግንኙነት መሻሻል ካለው ፋይዳ አንጻር ትልቅ ቦታ የሚሰጠው መሆኑም ተገልጿል።

የኳታሩ ኤሚር በኢትዮጵያ ከሁለት አመት በፊት ጉብኝት ያደረጉ ሲሆን፥ የየሃገራቱ ከፍተኛ ባለስልጣናትም በተለያየ ጊዜ የሁለትዮሽ ግንኙነቱን ለማጠናከር የሚያግዙ ጉብኝቶችን አካሂደዋል።

ከባለስልጣናቱ ጉብኝት ባለፈም ሃገራቱ በተለያዩ መስኮች በጋራ መስራት የሚያስችሉ የመግባቢያ ስምምነቶችን ፈጽመዋል።

ኢትዮጵያም በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች የተሰማሩ የኳታር ባለሃብቶች መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ ፍላጎት እንዳላት በተደጋጋሚ ስትገልጽ ቆይታለች።

ከዚህ ጋር ተያይዞም ባለፈው ጥር ወር በዶሃ  የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ፎረም መካሄዱ የሚታወስ ነው።

ፎረሙ በተያዘው የፈረንጆቹ አመት የሚካሄድ ሲሆን፥ ይህም የሃገራቱን የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነት ለማጠናከርና ለማሳደግ ያስችላል ተብሏል መባሉን ኤፍ ቢ ሲ ዘግቧል።

Related Articles

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Back to top button