Uncategorized

አሜሪካ የቦይንግ 737 ማክስ ኤይት አውሮፕላን ፈቃድ ላይ ምርመራ ልታደርግ መሆኑ ተሰማ

አሜሪካ የቦይንግ 737 ማክስ ኤይት አውሮፕላን ፈቃድ ላይ ምርመራ ልታደርግ መሆኑ ተሰማ

ሮይተርስ እንደዘገበው የአሜሪካ መንግሥት ቦይንግ 737 ማክስ ኤይት አውሮፕላን ለመብረር እንዴት ፈቃድ እንዳገኘ እንዲጣራ ትዕዛዝ አስተላልፏል።

ከመረጃ ሳጥኑ የተገኙት መረጃዎች ለኢትዮጵያዊያን መርማሪዎች የሚሰጥበት የመረጃ ልውውጥ ሂደቱም ቀጥሏል፡፡

በአምስት ወራት ውስጥ ሁለቴ የተከሰከሰው ይህ የቦይንግ ስሪት አውሮፕላን በኢትዮጵያው እና በኢንዶኔዢያው  አደጋዎቹ ውስጥ የቴክኒክ ችግር መመሳሰል አለ ከተባለ ወዲህ በአውሮፕላኑ ስሪት የቴክኒክ ጉዳዩች ላይ ጥርጣሬዎች እየተነሱ እንደሆነ ይታወቃል፡፡

የአሜሪካ የትራንስፖርት ሚንስትር ኤሊን ቻኦ የአሜሪካ ምርመራ ክፍል የአውሮፕላኑን የበረራ ፈቃድ እንዲያጣራ ጠይቀናል ብለዋል።

የአደጋው መርማሪዎች አንዱ ትኩረታቸውን ያደረጉት የአውሮፕላኑ ሞተር በድንገት ከመቆም የሚጠብቀውን ሥርዓት ማጥናት ሲሆን፤ አውሮፕላን አምራቹ ቦይንግ ደግሞ የሶፍትዌሩ መሻሻል ላይ እሰራለሁ እያለ ነው።

ቻኦ ለምርመራው ቡድን መሪ ካለቪን ስኮቭል በላኩት መልዕክት ምርመራው የአሜሪካ ፌደራል የአየር ትራንስፖርት አስተዳደር አውሮፕላኑ የበረራ ደህንነት ማረጋገጫ ምርመራ በትክክል እንደተካሄደበት ለማረጋገጥ እንዲረዳ የሚደረግ ነው ብለዋል።

የጥቅምት ወሩን የላየን ኤር አውሮፕላን አደጋ ተከትሎ ባለፈው የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ከተከሰከሰ በኋላ የአሜሪካ ፌደራል የአየር ትራንስፖርት አስተዳደር ለምን 737 ማክስ አውሮፕላንን ከበረራ ለማገድ ይህን ያህል ዘገየ የሚል ጥያቄ ፈጥሯል።

የአሜሪካ ፍትህ ቢሮ የፌደራል የአየር ትራንስፖርት አስተዳደሩ የቦይንግ አውሮፕላን የደህንነት ሁኔታን ለምን ችላ እንዳለ ምርመራ ጀምሯል ሲል ሮይተርስ አስነብቧል።

እንደሚባለው የአሜሪካ የፌደራል አቪዬሽን አስተዳደር የቦይንግ አውሮፕላኖች ሲከሰከሱ ለውሳኔ የዘገየው ዛሬ ብቻ አይደለም፡፡

በፈረንጆቹ 1965 እና 66 የቦይንግ 727 የተሰኙ አዳዲስ ምርቶች 3 ጊዜ የመከስከስ አደጋ ገጥሟቸው ነበር፡፡ ሁለቱ አደጋዎች የተከሰቱት አውሮፕላኖቹ ለማረፍ ሲሞክሩ ነበር፣ ሶስተኛው አደጋ ደግሞ ሁለቱ አውሮፕላኖች በተከሰከሱ በሶስተኛው ቀን ነበር የተከሰተው፡፡

ሲኤን ኤን በዘገባው እንዳለው በአሁኑ ደረጃ አውሮፓና ካናዳ የአውሮፕላኑን ደህንነት በራሳቸው ለማረጋገጥ መወሰናቸውን አሳውቀዋል ። ይህ ውሳኔም የአውሮፕላኑን ተመልሶ በዓለም አቀፍ ደረጃ የመብረር አቅም ጥያቄ ውስጥ ከትቶታል።

በተለመደው ሁኔታ ብዙውን ጊዜ አውሮፓውያንና ካናዳውያን የአደጋ መርማሪዎች የሚከተሉት የአሜሪካን ፌደራል የአየር ትራንስፖርት አስተዳደር የምርመራ ውጤት ነበር።

የአውሮፓ ህብረት የአየር ትራንስፖርት ደህንነት ኤጀንሲ /ኢሳ/ም በአውሮፕላኑ ላይ የሚደረጉትን ማንኛውም አይነት የንድፍ ማሻሻያ ስራዎች በጥልቀት ለመከታተል ቃል የገባ ሲሆን የኤጀንሲው ሃላፊ ፓትሪክ ኪ ሁሉንም ጥያቄዎቻችንን በበቂ ሁኔታ መልስ የሚሰጡ ነገሮችን ካላገኘን አውሮፕላኑ ተመልሶ እንዲበር ፈቃድ አንሰጥም ሲሉ  ለአውሮፓ ህብረት ማረጋገጫ ሰጥተዋል፡፡

የአሜሪካ ፌደራል የአየር ትራንስፖርት አስተዳደር በካናዳና አውሮፓ ህብረት ውሳኔ ላይ አስተያየት ከመስጠት ቢቆጠብም በመግለጫው አሁን በአሜሪካና በዓለም ላይ የሚታየው የበረራ ደህንነት እዚህ ስኬት ላይ የደረሰው በእኛ ጠንካራ ሥራ እና ከሌሎች የዓለም አየርመንገዶች ጋር በምናደርገው ትብብር ነው ብሏል።

ከአሜሪካ ቀድማ አውሮፕላኑን ከበረራ ያገደችው ካናዳ ፤ የአሜሪካን ፌደራል የአየር ትራንስፖርት አስተዳደር ማረጋገጫ ከመቀበል ይልቅ ወደፊት በራሷ መርምራ 737 ማክስ አውሮፕላንን የበረራ ፈቃድ እንደምትሰጥ አሳውቃለች።

 

የጨነቀው እንዲሉ ቦይንግ በበኩሉ  ለቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላን ዩኒቶች ያለባቸውን ችግር በቀጣይ ለመፍታት የሚረዳ አዲስ ሶፍትዌር ተግባራዊ ላደርግ ነው እያለ ነው፡፡

ቢቢሲ እንደዘገበው አዲሱ ሶፍትዌር የአውሮፕላን የቀዘፋ ስርአት የሚቆጣጠረውን አሰራር የሚገድብ ሲሆን  በአብራሪዎች ክፍል የማስጠንቀቂያ ስርዓት ላይ ለውጥ እንደሚያደርግም ቦይንግ አስታውቋል፡፡

ከዚህም ጎን ለጎን የበረራ ባለሙያዎች የሚሰለጥኑበት ሰነድ ወቅቱን የጠበቀ እና በኮምፒውተር የታገዘ እንዲሆን ይደረጋልም ብሏል፡፡

ባለፉት ሁለት አደጋዋች በአጠቃላይ 356 ሰዎች ሞተዋል። እስካሁን ሁለቱ አደጋዎች የተያያዙ መሆናቸውን የሚያረጋግጥ ማስረጃ ባይገኝም የኢትዮጵያን አውሮፕላን የመረጃ ሳጥን እየመረመሩ ያሉት የፈረንሳይ ባለሞያዎች እስካሁን ባላቸው ግኝት በሁለቱ አደጋዎች መካከል ተመሳሳይነት አለ ብለዋል።

ባለሙያዎች እንደሚሉት በቦይንግ አውሮፕላን ላይ አውሮፕላኑ ቁልቁል በአፍንጫው እንዳይከሰከስ ለማድረግ የተገጠመው አዲስ ቴክኖሎጂ ሁለቱም አደጋዎች ላይ ተፅዕኖ ሳይኖረው አይቀርም ።

 

ኢትዮጵያዊያን የአውሮፕላን አደጋ መርማሪዎች በፈረንሳዊያን ባለሙያዎች ያስገለበጡትን የበረራ ክፍል መቅረጸ ድምጽ መረጃ ይዘው ትላንት ወደ ሀገራቸው መመለሳቸውን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡

ከተከሰከሰው ቦይንግ አውሮፕላን 737 ማክስ 8 ካፒቴን ያሬድ ጌታቸው እና የበረራ ተቆጣጣሪ አሕመድ ኑር መሐመድ በአማርኛ ያደረጉትን የመረጃ ልውውጥ ያዳመጡት ኢትዮጵያዊያኑ መርማሪዎች ብቻ ናቸው ብሏል ሮይተርስ በዘገባው ፡፡

Related Articles

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Back to top button