Social

ላሊበላን ለመጠገን በፈረንሳይ መንግስት የተገባው ቃል አሁን ድረስ ተግባራዊ መሆን አልጀመረም

ላሊበላን ለመጠገን በፈረንሳይ መንግስት የተገባው ቃል አሁን ድረስ ተግባራዊ መሆን አልጀመረም

የላሊበላ አብያተ ክርስቲያናት ቅርሶች በመፍረስ አደጋ ውስጥ ስለሆኑ አፋጣኝ ጥገና ያስፈልጋቸዋል ተብሎ ከፍ ያለ እንቅስቃሴ ተጀምሮ ነበር። የአካባቢው ህዝብም ይህ ቅርስ ተረስቷል፣ እናድነው ብሎ ጉዳዩን መነጋገሪያ ለማድረግ ሰላማዊ ሰልፍ እስከመውጣት ደርሶ ነበር። አርትስ ቲቪ በቦታው ተገኝቶ ይህንኑ ጉዳይ ዘግቦ ነበር፡፡

የፈረንሳይ መንግስት ቅርሶቹን ለማደስ የሚያስፈልገውን ወጪ ለመሸፈን መስማማቱን ተከትሎ ባሳለፍነው መጋቢት 3  የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኤማኑኤል ማክሮን ለይፋዊ የስራ ጉብኝት ወደ ኢትዮጵያ በመጡበት ወቅት የፈረንሳይ የቅርስ ጥናት እና ምርምር ባለሞያዎች  የላሊበላ ውቅር አብያተክርስቲያናት እድሳት ስራቸውን በይፋ ጀምረዋል ሲሉ አብስረዋል፡፡

ለመሆኑ በአለም ቅርስነት የተመዘገበው የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት የእድሳት ጉዳይ ከምን ደረሰ  ሲል አርትስ ቲቪ በቦታው ተገኝቶ ስለሂደቱ የሚመለከታቸውን አካላት አነጋግሯል፡፡

የላሊበላ አብያተ ክርስቲያናት አናት ላይ ቅርሱን ከዝናብ እና ፀሃይ ይከላከላል ተብሎ በዩኔስኮ እና በጣሊያን መንግስት የተከለለው መጠለያ ለቅርሱ አደጋ ሆኗል ሲሉ የከተማዋ ነዋሪዎች በተደጋጋሚ ቅሬታቸውን አሰምተዋል፡፡

በያዝነው አመት ጥቅምት ወርም ከከተማዋ የተውጣጣ ኮሚቴ አዲስ አበባ ድረስ በመምጣት ም/ጠ/ሚ/ር ደመቀ መኮንንን አነጋግሯል። ይህንኑ ቅሬታም አቅርቧል። በዚህ በቅርሱ ጉዳት ዙሪያ አርትስ ቲቪም ተከታታይ ዘገባዎችን ወደናንተ ማድረሱ ይታወሳል።

በወቅቱ ም/ጠቅላይ ሚንስትር ደመቀ ያለፈው ጥቅምት ወር ሳያልቅ የገቢ ማሰባሰቢያ መድረክ ተዘጋጅቶ መጠለያውን ከአብያተክርስቲያናቱ ላይ ለማንሳትና ጥገናውን ለማከናወን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቅርስ ጥናት ባለሞያዎች ያስፈልጋል የተባለውን 300 ሚሊዮን ብር እንደሚያሰባሰብ ምላሽ መስጠታቸው ይታወሳል።

በሳምንታት ልዩነት ደግሞ ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አህመድ በስፍራው በመገኘት መንግሥት ቅርሱን እንደሚጠግን ለነዋሪዎቹ ቃል ገብተው ነበር። ይህን ተከትሎ ጠቅላይ ሚንስትሩ ወደ አውሮፓ ባመሩበት ወቅት ቅርሱ የሚጠገንበትን ድጋፍ ጠይቀው ከፈረንሳይ መንግሥት እሺታን አግኝተው ነበር የተመለሱት።

የተሰራውን ጊዜያዊ መጠለያ  ያያዘው  ምሰሶ የተተከለው በአብያተ ክርስቲያናቱ የውስጥ መተላለፊያ ዋሻ ላይ በመሆኑ እና ቅርሶቹ ያሉበት ቦታ መልከአምድራዊ አቀማመጡ ለአውሎ ንፋስ የተጋለጠ በመሆኑ ምሶሶው በንፋስ ሃይል በሚወዛወዝበት ጊዜ ምድሩን እየሰነጣጠቀው መሆኑን በቦታው ተገኝተን ተመልክተናል፡፡

በተጨማሪም መጠለያው  ጊዜያዊ ነው ተብሎ ለ 5 አመታት ብቻ ቢተከልም እንደቀልድ ለ11 ለአመታት የቆየ በመሆኑ ቅርሱ ዝናብና ጸሐይ ስለማያገኝ የአብያተክርስቲያናቱ  ጣሪያ ወደ አፈርነት እየተቀየረ እንደሆነ ነዋሪዎቹ ለ አርትስ ቲቪ ተናግረዋል፡፡

በአጠቃላይ የመጠለያው የአገልግሎት ዘመን ስላለቀ በቅርሱ ላይ ወድቆ አብያተ ክርስቲያናቱን ያወድማል የሚል ስጋት ነው ያለው፡፡

በአርኪዮሎጂ ዙሪያ ፈረንሳይ እና ኢትዯጵያ ትብብራቸውን ከጀመሩ ረጅም ዓመታትን አስቆጥረዋል። እ.አ.አ በ1950 ዎቹ አፄ ኃይለ ሥላሴ የአርኪዮሎጂ ክፍል ለመመሥረት ፈረንሳይ ኢትዮጵያን እንድታግዝ ጋብዘው ነበር።

ከዚያን ጊዜ አንስቶ የፈረንሳይ ድጋፍ በተለይ በአርኪዮሎጂና ታሪክ ረገድ ኢትዮጵያን አልተለያትም። ፕሬዚዳንት ኤማኑኤል ማክሮን ከመጋቢት 3 ጀምሮ ለሁለት ቀን ይፋዊ ጉብኝት ለማድረግ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ በመጡበት ወቅት ጉብኝታቸውን የጀመሩትም መንገስታቸው ሊጠግነው ፍቃዱን ከሰጠበት ላሊበላ ነበር፡፡

ፈረንሳይ የገባችው ቃል ከምን ደረሰ; አሁንስ የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት የእድሳት እና መጠለያዎቹን የማንሳቱ ጉዳይ ምን ደረጃ ላይ ነው ሲል አርትስ ጠይቋል;

የፕሮጀክቱ መሪዎች  ማሪ ሎር ዴራ እና ክሌር ቦሽ ቲዬሴ የሚባሉ የታሪክና አርኪዎሎጂ ተመራማሪ ሴቶች መሆናቸውን አርትስ ለማወቅ ችሏል።

ባለሞያዎቹ ተጨማሪ ጥናት ያስፈልጋል ይበሉ እንጂ የባህል እና ቱሪዝም ሚኒስትሯ ዶ/ር ሂሩት ካሳው  ግን ቀደም ባለ ገለጻቸው ፈረንሳዮቹ ቃል ከገቡበት ጊዜ ጀምረው በትኩረት እየሰሩ ነው ይላሉ። ፈረንሳዮቹ በግላቸው የ10 አመት ጥናት ስለነበራቸው ለኛ አቅርበውልን ከሃገር ውስጥ ሙያተኞች ጥናት ጋር ተመሳሳይ በመሆኑ ቀጣይ ስራዎችን እየሰራን ነው ብለውነበር፡፡

አሁን ግን ተጨማሪ ጥናት እየተጠበቀ መሆኑን ነው ባለሞያዎቹ የሚናገሩት፡፡

መጠለያዎቹም አሁንም አልተነሱም ። ቅርሱም አሁን ድረስ በተመሳሳይ ሁኔታ ላይ ነው የሚገኘው፡፡

አለም ሁሉ የሚደመምባቸው ከድንጋይ የተፈለፈሉ፣ አስደናቂ የኪነ ህንፃጥበብ የሚታይባቸው የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት  ከ900 አመት በፊት ነው  በኢትዮጵያውያን የተሰሩት፡፡

በኢትዮጵያውያን የተሰራውን ሳይፈርስ ለመጠበቅና በእድሜ ብዛት ያረጀውን ቅርስ ለማደስ አሁንም ግን የአውሮፓውያን እርጥባን እየተጠበቀ ነው።

Related Articles

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Back to top button