loading
ጠቅላይ ሚኒስትር ቴሬዛ ሜይ የብሪታኒያ የፓርላማ አባላት የብሬግዚትን ጉዳይ በድጋሜ እንዲያጤኑት አሳሰቡ

ሜይ ይህንን ያሉት ብሪታኒያ ከአውሮፓ ህብረት አባልነቷ ለመውጣት በምታደርገው ጥረት፤ ከህብረቱ መሪዎች ጋር ባደረጉት ውይይት ነው፡፡

በውይይቱ ብሪታኒያ ከህብረቱ ለመውጣት የማያዳግም መፍትሄ እንድታሳልፍ፤ ተጨማሪ የሁለት ሳምንታት ዕድሜ ከመሪዎቹ ማግኘት ችለዋል፡፡

ሀገሪቱ ከአውሮፓ ህብረት የመውጫ ጊዜ ከሰባት ቀናት በኋላ የሚጠናቀቅ ቢሆንም፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ቴሬዛ ሜይ ግን ከሀገሪቱ የፓርላማ አባላት በኩል፤ ውሳኔውን በማዘግይታቸው ደጅ መጥናታቸው ሳያሰለቻቸው አይቀርም፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሯ ሁሉም ነገር አልጋ በአልጋ ሆኖላቸው፤ የፓርላማ አባላቱን ይሁንታ በሚቀጥለው ሳምንት ቢያገኙ እንኳ፤ አጠቃላይ የህግ ማውጣት ሂደት እስኪጠናቀቅ ድረስ፤ ብሪታኒያ እስከ ግንቦት 22/2019 የህብረቱ አባል ሁና መቀጠሏ አይቀርላትም፡፡

ይሁንና ቴሬዛ አሁንም የፓርላማ አባላቱን የስምምነት ድምፅ የማያገኙ ከሆነ፤ ሚያዚያ 12 የአውሮፓ ህብረት አባል ሀገራት ፊት ቆመው መለመናቸው አይቀርም ተብሏል፡፡

የህብረቱ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ተስክ ‹‹ ሁሉም የብሬግዚት አማራጮች እስከ ሚያዚያ 12 ድረስ ክፍት ናቸው›› ብለዋል፡፡

ይህ ሁሉ ከመሆኑ አስቀድሞ ግን፤ ቴሬዛ ሜይ የብሪታኒያ የፓርላማ አባላት ከህብረቱ በኩል የተሰጣቸውን የእፎይታ ጊዜ በመጠቀም፤ እሳቸው የሚያቀርቡትን አዲስ የስምምነት ውል በደንብ አጢነው ድምፃቸውን እንዲሰጧቸው አሳስበዋል፡፡

ከማሳሰቢያው ጎን ግን እባካችሁ ስምምነቱ ይሰምር ዘንድ በጋራ እንስራ በማለት ተማፅኗቸውን አሰምተዋል፡፡

እንደ ቢቢሲ ዘገባ ለሶስተኛ ጊዜ በሚቀርበው የብሬግዚት ህግጋት፤ በፓርላማ አባላቱ ዘንድ ተቀባይነት የሚያገኝ ይመስላል፡፡

Write a Reply or Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *