loading
ባርሴሎና በጠባብ ውጤት ሲረታ፤ ዩቬንቱስ አቻ ተለያይቷል

በአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ የሩብ ፍፃሜ የመጀመሪያ ጨዋታ ትናንት ምሽት ሁለት ግጥሚያዎች ተከናውነዋል፡፡

ወደ እንግሊዝ ምድር የመጣው የስፔኑ ሃያል ክለብ ባርሴሎና በኦልድ ትራፎርድ ማንችስተር ዩናይትድን 1 ለ 0 በሆነ ጠባብ ውጤት በመርታት መልካም ውጤት አስመዝግቧል፡፡

ዩሯጓያዊው አጥቂ ሊዩስ ሱዋሬዝ ከሊዮኔል ሜሲ የተሻገረለትን ኳስ በግንባሩ በመግጨት ወደ ግብ የላካት ኳስ በተከላካዩ ሉክ ሻው ተጨርፋ ዳቪድ ዴ ሂያ መረብ ላይ አርፋለች፡፡

ባርሳ ሰፊውን የጨዋታ ክፍለ ጊዜ የተቆጣጠረ በመሆኑ ከዚህ በላቀ የግብ ልዩነት ያሸንፋል ተብሎ ግምት ቢሰጥም፤ ተጨማሪ ግብ ሳያስቆጥር ጨዋታውን በዚሁ ውጤት አጠናቅቋል፡፡

ቀያይ ሰይጣኖቹ አንዳንዴ ከሚያደርጓቸው ግብ የማግባት እንቅስቃሴዎች ውጭ፤ ይሄን ያህል አስፈሪ የሚባል ኢላማውን የጠበቀ ኳስ ወደ ቴርስቴገን መረብ ሳይልኩ አምሽተዋል፡፡ ቡድኑ እንደ አማራጭም የመልሶ ማጥቃት እና የባርሳ ስህተቶችን መጠቀም ያለመ እንቅስቃሴ ሲያደርግ ተስተውሏል፡፡

የኦሌ ቡድን ውጤቱን በመልሱ ጨዋታ ለመቀልበስ አስቸጋሪ ባይሆንበትም፤ ፒ.ኤስ.ጂ ላይ የፈፀመውን ገድል ካምፕ ኑ ላይ ይደግማል ለማለት የሚያስቸግር ይሆናል፡፡

በሌላኛው የተመሳሳይ ሰዓት ጨዋታ ደግሞ የጣሊያኑ ዩቬንቱስ ወደ ኔዘርላንድ አምርቶ አምስተርዳም ላይ ከአያክስ ጋር በ1 ለ 1 አቻ ውጤት ተለያይቶ ተመልሷል፡፡

አያክሶች የጨዋታውን ሙሉ እንቅስቃሴ በቁጥጥራቸው ስር አድርገው ባመሹበት ፍልሚያ፤ የመጀመሪያው አጋማሽ ከመጠናቀቁ በፊት ከጆ ካንሴሎ የተገኘችውን ኳስ ፖርቱጋዊው ክርስቲያ ሮናልዶ በጭንቅላቱ በመግጨት አሮጊቷን መሪ ማድረግ ችሏል፡፡

ይህቺ ግብ ሮናልዶ በቻምፒዪንስ ሊግ ያስቆጠራቸውን የግብ ብዛት መጠን ወደ 125 ያደረሰች ሁናለች፡፡

የሁለተኛው አጋማሽ እንደተጀመረ ባለሜዳዎቹ ያስተናገዱት ግብ ጫና ሳያሳድርባቸው ፈጣን ምላሽ በዳቪድ ኔሬስ አማካኝነት በመስጠት አቻ መሆን ችለዋል፡፡

አያክስ በሙሉ ጨዋታው በተደጋጋሚ የዩቬ የግብ ክልል ውስጥ እየገቡ የግብ ሙከራዎችን ማድረግ ባይችሉም ተጨማሪ ግብ ሳያስቆጥሩ ወጥተዋል፡፡

በመልሱ የቱሪን ግጥሚያ የሁለቱ ጨዋታ ተጠባቂ ነው፡፡

ትናንት ምሽት ጨዋታቸውን ያደረጉ ቡድኖች የመልስ ግጥሚያቸውን ቀጣይ ሳምንት ማክሰኞ ያደርጋሉ፡፡  

Write a Reply or Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *