loading
በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የሊጉ መሪዎች ሽንፈት አስተናግደዋል

የ20ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በርካታ ጨዋታዎች በትናንትናው ዕለት ተከናውነዋል፡፡

የእለቱ ማሳረጊያ ጨዋታ አዲስ አበባ ስታዲየም ላይ ሲከናወን ፤ ቅዱስ ጊዮርጊስ የደቡቡን ሲዳማ ቡና አስተናግዶ የ2 ለ 0 ድል አስመዝግቦ ከሊጉ መሪዎች ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት አጥብቧል፡፡

በጨዋታው የመጀመሪያው ክፍለ ጊዜ ቅዱስ ጊዮርጊስ የተሻለ የነበረ ቢሆንም ቅድሚያ ወደ ጎል ሙከራ ማድረግ የቻሉት ሲዳማዎች ነበሩ፤ ምንም ኢላማውን የጠበቀ ባይሆንም፡፡

ከ10ኛው ደቂቃ በኋላ የፈረሰኞቹ ተጫዋቾች ወደ ተጋጣሚያቸው የግብ ክልል በተደጋጋሚ በመድረስ የጎል ሙከራዎችን አድርገዋል ፤ በተለይ ወጣቱ አቤል ያለው 20ኛው እና 32ኛው ደቂቃ ላይ ያመከናቸው ኳሶች ለቡድኑ የሚያስቆጩ ነበሩ፡፡

ከተደጋጋሚ ሙከራ በኋላ ጊዮርጊሶች 35ኛው ደቂቃ ላይ አቤል ከማዕዘን ያሻማትን ኳስ በኢሱፍ ቡርሃና ግንባር ተገጭታ ወደ ግብነት ተቀይራለች፡፡

ከግቧ መቆጠር በኋላ ባለሜዳዎቹ ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር ሙከራ አድርገው አልተሳካላቸውም፡፡

ከዕረፍት መልስ ቅዱስ ጊዮርጊስ በተጋጣሚያቸው ላይ ጫና በመፍጠር ግብ ለማከል እንቅስቃሴ ቢያደርጉም ፤ ውጤታማ መሆን አልቻሉም፡፡

በዚህ መሀል ከ70 ደቂቃዎች በኋላ የሲዳማው አዲስ ግደይ በጊዮርጊሱ ሄኖክ አዱኛ ጥፋት ተሰርቶበታል እና ፍፁም ቅጣት ምት ይገባናል ያሉት የእንግዳው ቡድን ተጫዋቾች ከአርቢትር እያሱ ፈንቴ ጋር ረዘም ያለ ክርክር በማድረጋቸው ምክንያት ጨዋታው ተቋርጦ ነበር፡፡

የአርቢትሩ ውሳኔ ለሲዳማ ተጫዋቾች የማስጠንቀቂያ ካርድ በማሳየት፤ ጨዋታው የቀጠለ ሲሆን ተቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው አሜ መሀመድ በተከታታይ ሁለት ግብ የሚሆኑ ሙከራዎችን ቢያከናውንም ፤ በግቡ አግዳሚ ፖል እና በሲዳማው ግብ ጠባቂ ፍቅሩ ወዴሳ ግብ ከመሆን ድነዋል፡፡

በዚሁ ጫና የገፉት ፈረሰኞቹ 83ኛው ደቂቃ ላይ የሲዳማው ተከላካይ ሰንደይ ሙቱኩ በተዘናጋበት ቅፅበት ከፍሪምፖንግ ሜንሱ የተሻገረችውን ኳስ አቡበከር ሳኒ በግንባሩ ገጭቶ በማስቆጠር የቡድኑን መሪነት ወደ ሁለት ከፍ አድርጓል፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ ጠንካራ ሙከራዎች እንኳ ማድረግ የተሳነው የደቡቡ ቡድን ፤ የጨዋታው መገባደጃ አካባቢ በወንድሜነህ አይናለም ወደ ግብ የተላከችው ኳስ በፓትሪክ ማታሲ ቁጥጥር ስር ውላለች፡፡  

ጊዮርጊስ በደጋፊዎቹ ድጋፍ ታጅቦ ፤ የጨዋታውን የበላይነት ወስዶ አሸናፊ በነበረበት ግጥሚያ ሶስት ነጥብ ማሳካቱን ተከትሎ ያለውን የነጥብ መጠን ወደ 33 ከፍ አድርጓል፡፡ አራተኛ ደረጃ ላይም ተቀምጧል፡፡

የሊጉ አናት ላይ የሚገኘው መቐለ 70 እንደርታ በባህር ዳር ከነማ የ1 ለ 0 ድል ሽንፈት ማስተናገዱን ተከትሎ ያለው የነጥብ ልዩነት 9 ሁኗል፡፡ መቐለ አሁንም በሊጉ የደረጃ ሰንጠራዥ ላይ በ42 ነጥብ ቀዳሚ ነው፡፡

በሳምንቱ በአቻ ውጤት በብቸኝነት በተጠናቀቀው ጨዋታ ፋሲል ከነማ ጎንደር ላይ ከደቡብ ፖሊስ በ1 ለ 1 አቻ ውጤት አጠናቅቋል፤ አፄዎቹ አንድ ነጥብ ማሳካታቸው ወደ ሁለተኛ ደረጃ ከፍ እንዲሉ ሁኗል ከሲዳማ ቡና ዕኩል 34 ነጥቦችን ይዞ በግብ ክፍያ በመብለጥ፡፡

በሌሎች የክልል ላይ ስታዲየሞች ጨዋታ፤ ወደ ሶዶ የተጓዘው ኢትዮጵያ ቡና በአሰልጣኝ አሸናፊ በቀለው ወላይታ ድቻ 2 ለ 1 ተረትቷል፤ አዳማ ከተማ ደግሞ ሜዳው እና ደጋፊው ላይ በሀዋሳን የ2 ለ 1 ሽንፈት ገጥሞታል፡፡

በርካታ ግቦች በተመዘገበበት ግጥሚያ ድሬዳዋ ከነማ ትግራይ ላይ ደደቢትን 3 ለ 2 ድል አድርጓል፡፡

ጅማ አባ ጅፋር ደግሞ ጅማ ላይ ተጋጣሚውን ስሑል ሽረ 2 ለ 0 መርታት ችሏል፡፡ 

ቅዳሜ ዕለት ወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ ትግራይ ላይ መከላከያን 1 ለ 0 በመርታት በሊጉ ያለውን ደረጃ ወደ 7ኛ ከፍ አድርጓል፡፡

መከላከያ፣ ስሑል ሽረ እና ደደቢት ወረጅ ቀጠና ውስጥ ተቀምጠዋል፡፡

Write a Reply or Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *