loading
ፒያሳ ላይ ከሚድሮክ የተመለሰው ቦታ የአድዋን ታሪክ የሚዘክር ሙዚየም ሊገነባበት ነው፡፡

ፒያሳ ላይ ከሚድሮክ የተመለሰው ቦታ የአድዋን ታሪክ የሚዘክር ሙዚየም ሊገነባበት ነው፡፡

ይህን የጥቁር ህዝቦችን ታሪክ የሚያስታውስ ማእከል የሚገነባው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ነው፡፡

ማእከሉ የሚገነባው የአድዋ ድል ለመጪው ትውልድ ከቃላዊ ንግግር ፣ከፅሁፍ ሰነድ እና ከምስል መረጃ ባሻገር  ከህዝብ ጋር ዘመን በሚሻገር እና በሚዳሰስ ቅርስ በሙዚየም መልክ ቢደራጅ ከፍ ያለ ጠቀሜታ ስለሚኖረው ነው ተብሏል፡፡

አስተዳደሩ ይህን ማእከል የሃገራች ከተሞች ርቀት መነሻ ቦታ ዜሮ ኪሎሜትር በሆነው በጥንታዊ መጠርያው ሲኒማ አድዋ በመባል በሚታወቀው ቦታ ላይ ለመገንባት ምክረ ሃሳብ አዘጋጅቷል፡፡

በምክረ-ሃሳቡ ላይ የታሪክ ምሁራን ፣ የኪነ-ህንፃ ባለሞያዎች እና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በመነሻ ሃሳቡ ላይ አስተያየታቸውን እየሰጡ ነው፡፡

በጋሻ መልክ ሚነገባው ማዕከል ተገንብቶ ሲያልቅ “ሁሉም ከዚህ ይጀምራል!” የሚል የአዲስ አበባ ከተማ ‘ዜሮ ኪሎ ሜትር’ ምልክት ይቀመጥበታል፡፡

ማዕከሉ ግንባታው ሲጠናቀቅ በውስጡ ቤተ-መፅሃፍት ፣ ቤተ-ስዕል ፣ የህፃናት ማቆያ ፣ የክዋነ-ጥበባትና የሲኒማ አዳራሽ ፣ የስፖርት ማዘውተርያዎች ፣ ሱቆች ፣ ካፌዎች እና የምግብ አገልግሎት መስጫ ተቋማት የሚኖሩት ይሆናል፡፡

ይህ ሊገነባ የታሰበው ማዕከል ከሚኖረው ማህበረ-ባህላዊ ፋይዳ በተጨማሪ በውስጡ በጊዜው የነበሩ አልባሳት ፣ ጥቅም ላይ የዋሉ የጦር መሳርያዎች ፣ ከቅስቀሳው ጀምሮ እስከ ጦር አውዱ የተዘገቡ ማናቸውም ጉዳዮች የሚሰነዱበት እና ለዕይታ የሚበቁበት ስፍራ ይሆናል፡፡

የማዕከሉ የውጪ ይዞታም ለመዝናኛ የተመቸ ለቱሪስት መስህብነት የሚያገለግል ሲሆን አረንጓዴ እና ነፋሻማ የሆነ አከባቢን በመፍጠሩ ሂደትም ጉልህ ሚና ይኖረዋል፡፡

የማዕከሉ ግንባታ በህዝቦች መካከል ከልዩነት ይልቅ አንድነት እንዲጠነክር አገራቸውን በጋራ እንዲገነቡ ታላቅ መነሳሳትን ይፈጥራል ነው የተባለው።

ይህ ማዕከል የመላው ኢትዮጵያዊያን በመሆኑ ለመነሻ በቀረበው ምክረ ሃሳብ ላይ ህብረተሰቡ የራሱን ሃሳብ እንዲሰጥበት አስተዳደሩ ጥሪ አቅርቧል፡፡

 

Write a Reply or Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *