loading
ኢትዮጵያ በሚዲያ ነፃነት 40 ደረጃዎች ማሻሻሏን ድንበር የለሽ የጋዜጠኞች ቡድን አስታወቀ

ኢትዮጵያ በሚዲያ ነፃነት 40 ደረጃዎች ማሻሻሏን ድንበር የለሽ የጋዜጠኞች ቡድን አስታወቀ

አለም አቀፉ ድንበር የለሽ የጋዜጠኞች ቡድን በኢትዮጵያ ያለው የሚዲያ ነፃነት ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር 40 ደረጃዎች ማሻሻሉን ገለፀ።

መቀመጫውን ፈረንሳይ ያደረገው የዓለም አቀፉ ድንበር የለሽ የጋዜጠኞች ቡድን ዓመታዊውን ዓለም አቀፍ የሚዲያ ነፃነት መለኪያ የደረጃ ሰንጠረዥን ይፋ አድርጓል።

በዚህ መሰረትም ኢትዮጵያ ከ180 ሀገሮች መካከል ባለፈው ዓመት ከነበረችበት 150ኛ ደረጃ ላይ 40 ደረጃዎችን በማሻሻል 110ኛ መሆኗን አስታውቋል።

ኢትዮጵያ ደረጃዋን ያሻሻለችውም በቅርቡ ጠቅላይ ሚነስትር ዶክተር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን መምጣታቸውን ተከትሎ በሀገሪቱ በተከሰተው የለውጥ ሂድት በሀገሪቱ የመገናኛ ብዙሃን ላይ ከፍተኛ የሆነ የሚዲያ ነፃነት በመስተዋሉ ነው ተብሏል።

ይህን ተከትሎም በኢትዮጵያ ታስረው የነበሩ በርካታ ጋዜጠኞችና ጦማሪያን መፈታታቸውን እና ተዘግተው የነበሩ በርካታ ድረ ገጾች መከፈታቸውን በማሳያነት ጠቅሷል።

ከዚህ ባለፈም በሀገሪቱ ሃሳብን በነፃነት መግለፅ ይከለክሉ የነበሩ አፋኝ ህጎች መሻሻላቸውን አስታውቋል።

በተጨማሪም ባለፉት አስርት ዓመታት በሀገሪቱ ለመጀመሪያ ጊዜ ከፈረንጆቹ 2018 መጨረሻ ላይ ጀምሮ የታሰረ ጋዜጠኛ አለመኖሩን አንስቷል።

አለም አቀፉ ድንበር የለሽ የጋዜጠኞች ቡድን የሚዲያ ነፃነት መለኪያ በየዓመቱ 180 ሀገሮች ላይ ያለውን የሚዲያ ነፃነት የሚመረምር ድርጅት ነው።

በዚህ ዓመት የሚከበረው የዓለም የሚዲያ ነፃነት ቀን ጉባኤም የፊታችን ሚያዚያ 24 እና 25 ቀን 2011 ዓ.ም በአዲስ አበባ ይካሄዳል ።

ጉባኤው መገናኛ ብዙሃን ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን ለመገንባትና ነፃ ምርጫ ለማካሄድ ያላቸው ሚና ላይ ትኩረቱን ያደርጋል ተብሏል።

በጉባኤውም 1 ሺህ 500 በላይ የሚሆኑ ከተለያዩ ሀገራት መንግስታትና እና አለም አቀፍ የግል ድርጅቶች የተውጣጡ ተወካዮች ይሳተፋሉ ተብሎይጠበቃል ሲል ኤፍቢሲ ዘግቧል።

 

Write a Reply or Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *