loading
የጅቡቲ-ገላፊ እና የታጁራ-በልሆ መንገዶች ግንባታ እየተፋጠነ ነው

የጅቡቲ-ገላፊ እና የታጁራ-በልሆ መንገዶች ግንባታ እየተፋጠነ ነው

የጅቡቲ የትራንስፖርት ሚኒስትር ሞሃመድ አብዱልካድር የጅቡቲ-ገላፊ እና የታጁራ-በልሆ መንገዶች ግንባታን አስመልክቶ ከተቋቋመው የአገሪቱ የቴክኒክ ኮሚቴ ጋር ውይይት አድርገዋል።

በውይይቱ ለአሽከርካሪዎች አስቸጋሪ መንገድ የሆነውን የዲኪል-ጋላፊ መንገድ እንዲሁም የታጁራ-በልሆ መንገድ ግንባታን አስመልክቶ ጥናቶች የቀረቡ ሲሆን በጥናቶቹ መሰረት የዲኪል-ገላፊ መንገድ ግንባታ በአጭር ጊዜ ውስጥ ጨረታ በማውጣት ወደ ስራ የሚገባበት መንገድ ተጠቁሟል፡፡

የትራንስፖርት ሚኒስትሩ ሞሃመድ አብዱልካድር እንዳሉት የመንገዶቹ ግንባታ መጠናቀቅ የአሽከርካሪዎች ደህንነት ከመጠበቅ ባሻገር የኢትዮጵያንና የጅቡቲን ብሎም የቀጠናውን የኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተራክቦ ከፍ ወዳለ ደረጃ እንደሚያሳድገው ገልጸዋል፡፡

በኢንቨስትመንት ጉዳዮች የአገሪቱ ፕሬዚዳንት አማካሪ ፋሃሚ አል ሃግ ፣ የትራንስፖርት ሚኒስትሩ የቴክኒክ ጉዳዮች አማካሪ አህመድ አብዶ አሊ እና ሌሎች ሃላፊዎችም በስብሰባው ተገኝተዋል ሲል የውጭ ጉዳይ ቃል አቀባይ ፅህፈት ቤት አስታውቋል።

የትራንስፖርት ሚኒስትሩ አክለውም ቀሪው የታጁራ-በልሆ መንገድ በቅርቡ እንደሚጠናቀቅ ገልጸው ለመንገዶቹ ግንባታ የገንዘብ እገዛ ያደረጉትን የሳዑዲ-አረቢያ እና የጃፓን መንግስታት አመስግነዋል፡፡

በ15ኛው የኢትዮ-ጅቡቲ የጋራ የሚኒስትሮች ኮሚሽን ስብሰባ ወቅት የመንገዶቹ ግንባታ በአፋጣኝ መጠናቀቅ የሚቻልባቸው መንገዶች ላይ የሁለቱ አገራት ከፍተኛ ኃላፊዎች መምከራቸውና አቅጣጫዎች መቀመጣቸው የሚታወስ ሲሆን ጅቡቲ በሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ በኩል ክትትሎች እየተደረጉ መሆኑን መረዳት ተችሏል፡፡

 

 

 

 

Write a Reply or Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *